ለራያ ዩኒቨርሲቲ ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎች የህይወት ልምድ ማጋራት መርሃ ግብር (Motivational Forum) ተካሄደ

የራያ ዩኒቨርሲቲ የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ባዘጋጀው የህይወት ልምድ ማጋራት መርሃ ግብር (Motivational Forum) በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሃፍቱ በርሀ የትምህርት፣ ምርምር፣ ማህበረሰብ አገልግሎት፣ ዙርያ ያበረከቷቸው ውጤታማ ስራዎች ዛሬ ህዳር 14.2017 ዓ.ም ለህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎች ልምዳቸውን አካፍለዋል።
በመርሃ ግብሩ የራያ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕረዚደንትን በመወከል መምህር ህንፃ ገ/ጊዮርጊስ (ረዳት ፕሮፌሰር) ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ ራያ ዩኒቨርሲቲ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለመክፈት ስርዓተ ትምህርት (Curriculum) ቀርፆ፣ በ2012 ዓ.ም ደግሞ የሕክምና ቁሳቁስ አሟልቶ፣ በ2015 ዓ.ም በህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ስር የነርሲንግ (Nursing)፣ ሚድዋፍሪ (Midwifery) እና ሜዲካል ላብራቶሪ (Medical Laboratory Science) ትምህርት ክፍሎች ማስተማር ጀምሯል፤ በማለት ለተማሪዎቻችን እንደዚህ ዓይነት የህይወት ማጋራት መርሃ ግብር (Motivational Forum) ትልቅ ፋይዳ ስላለው በትኩረት መከታተል እና መተግበር ይጠበቅባችኋል ብለዋል።
ፕሮፌሰር ሃፍቱ በርሀ የህይወት ተሞክሯቸውን በማንሳት በርካታ ውጣ ውረድ ያለበት የስራ ህይወት ምዕራፍ አሳልፈው ለዚሁ ስኬት መብቃታቸው ለተማሪዎች ጥሩ ተሞክሮ እንደሆነ እና ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ይሁን በስራ ዓለም ውጤታማ ለመሆን የሚያስችሏቸው የውጤት መንገዶች (Motivations)፣ ጤናማ አስተሳሰብ፣ የህይወት ግብ፣ ውጤታማ የጊዜ አጠቃቀም፣ ስኬትን ማስቀጠል እንዲሁም ሌሎች የህይወት ክህሎቶች በዝርዝር ገለፃ አድርገዋል።
በመርሃ ግብሩ የተሳተፉ የዩኒቨርሲቲው ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎች በበኩላቸው ከፕሮፌሰር ሃፍቱ በርሀ ያገኙት የህይወት ልምድ ማጋራት መርሃ ግብር አመስግነው ተማሪዎች ራሳቸውን ያሉበትን ሁኔታ ለማየት እና ለቀጣይም ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ስንቅ የሰነቁበት እንደነበር ተናግረዋል።
በመጨረሻም የራያ ዩኒቨርሲቲ ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን መምህር ስብሃት ገ/ህይወት (ረዳት ፕሮፌሰር) በመዝጊያ ንግግራቸው፤ ፕሮፌሰር ሃፍቱ በርሀ ለተማሪዎቻችን ያካፈሉት ህይወትን የሚቀይር ስኬታማ የስራ ህይወት አመስግነው ተማሪዎች ያገኛችሁት የህይወት ልምድ ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ የትምህርት እና ስራ ህይወት እንዲኖራችሁ እና በእውቀታችሁ እና ክህሎታችሁ ህዝባችሁ እና ሃገራችሁን ለማገልገል ይረዳችኋል ብለዋል።

ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ሕዳር 14 ቀን 2017 ዓ.ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
*****************************************