ራያ ዩኒቨርሲቲ ከብሄራዊ ቤተ-መጻህፍትና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በተለያየ ደረጃ ለሚገኙ የዩኒቨርሲቲው ቤተ-መጻሕፍትና ቤተ-መዛግብት ሰራተኞች ከጥቅምት 20-30/2017 ዓ/ም ለተከታታይ አስር ቀናት ሲሰጥ የቆየው መሰረታዊ የቤተ-መጻሕፍት ሳይንስ እና ዲጂታላይዜሽን ስልጠና ዛሬ ጥቅምት 30/2017 ዓ/ም ተጠናቀቀ።
የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር እና ልማት ምክትል ፕረዚደንት ዶ/ር ክብሮም ካሕሱ በስልጠናው መዝጊያ መርሃ ግብር እንደተናገሩት፤ አዳዲስ የቤተ-መጽሐፍትና ቤተ-መዛግብት እውቀት፣ ቴክኖሎጂዎችና ዲጂታላይዜሽን ስርዓት ትግበራ የሚያረጋግጥ፣ የሰራተኞች እውቀት እና ክህሎት ክፍተት የሚሞላ እንዲሁም የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ የሚያግዝ የክልሰ ሐሳብ እና ተግባር ተኮር ስልጠና ለሰጡ አሰልጣኞች አመስግነው በቀጣይም ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተ-መጻሕፍትና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ ያለውን ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ስልጠናውን የሰጡት ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተ-መጻሕፍትና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ የመጡ ባለሙያዎች አቶ እስራኤል ብዙ እና አቶ ስለሺ ወርቁ ሲሆኑ በስልጠናው መዝጊያ መርሃ ግብር፤ ዩኒቨርሲቲው ላደረገላቸው ቀና ትብብር እና ሰልጣኞች ለነበራቸው ንቁ ተሳትፎ በማመስገን ተግባር ተኮር ስልጠናው ብዙ ትምህርት የተገኘበት እና ለቤተ-መጻሕፍትና ቤተ-መዛግብት ትልቅ አስተዋፅኦ ያላቸው መተግበሪያዎች (Softwares) የተጠቀምንበት ነበር ብለዋል።
አሰልጣኞቹ አክለው ለቤተ-መጻሕፍትና ቤተ-መዛግብት ትኩረት ቢደረግ፣ ተመሳሳይ መጻሐፍ በብዛት ኮፒ ባይገዙ እና ተገቢ ሰራተኛ ወደ ቤተ-መጻሕፍትና ቤተ-መዛግብት እንዲመደቡ መደረግ አለበት በማለት ሙያዊ ምክራቸውን ለግሰዋል።
ሰልጣኞች በበኩላቸው ራያ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተ-መጻሕፍትና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ለተሰጣቸው ተግባር ተኮር ስልጠና አመስገነው ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት እና ክህሎት ጥራት ያለው የቤተ-መጻሕፍትና ቤተ-መዛግብት አገልግሎት ለመስጠት ይረዳናል ብለዋል።
በተጨማሪም ሰልጣኞቹ፤ ለቤተ-መጻህፍት እና ቤተ-መዛግብት ሰራተኞች ትኩረት ቢሰጥ ከዚህ የበለጠ ውጤታማ ስራ ሊሰራ ይችላል በማለት ሃሳባቸውን አቅርበዋል።
በመጨረሻም ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተ-መጻሕፍትና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ እና ለአሰልጣኞቹ በዶ/ር ክብሮም ካሕሱ እና ዶ/ር መሐመድአወል የሱፍ (የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕረዚደንት ልዩ ረዳት) የምስጋና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።
********************************************
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ጥቅምት 30/ 2017 ዓ/ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
********************************************