ራያ ዩኒቨርሲቲ ለሚቀበላቸው የ9ኛ ክፍል ተማሪዎች የመግቢያ ፈተና በተሳካ ሁኔታ ሰጥቷል።

ዩኒቨርሲቲው በ2017 ዓ/ም ልዩ ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት እና የጋርዮሽ ሳይንስ መርሃ-ግብር (Science Shared Program) የ9ኛ ክፍል ተማሪዎች ተቀብሎ ለማስተማር የመግቢያ ፈተና ዛሬ መስከረም 07/2017 ዓ/ም በተሳካ ሁኔታ ሰጥቷል።
የራያ ዩኒቨርሲቲ ፕረዚደንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ በፈተናው ስነ-ስርዓት ባስተላለፉት መልእክት መሰረት ትምህርት የማህበራዊ፣ ስነ ልቦናዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ለመፍታት እንደ ቁልፍ መሳርያ በመሆኑ ራያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በዕውቀት፣ ክህሎት እና ግብረ-ገብ (Ethics) የታነፀ ዜጋ ለማፍራት ውጤታማ ስትራቴጂያዊ ስራዎች በመስራት ችግር ፈቺ ብቁ ዜጋዎች ለማፍራት የተቀናጀ ስራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የራያ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕረዚደንት ነጋ ዓፈራ (ዶ/ር) በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ በ2017 ዓ/ም የሠማእታት መታሰብያ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት መደበኛ የመማር ማስተማር ስራውን ለመጀመር የካቲት 01/2016 ዓ/ም በወሰነው መሰረት አዳሪ ትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ተመድቦለት፣ አስፈላጊውን የመማርያ ክፍል፣ ቤተ-መፃህፍት፣ ዲጂታል መማርያ ክፍል፣ መኖርያ ህንፃ፣ ምግብ እና ሌሎች አስፈላጊውን አገልግሎቶች አሟልቶ በ8ኛ ክፍል ከፍተኛ ውጤት ያመጡ በዕውቀት፣ ክህሎት እና ስነ ምግባር ምጡቅ የሆኑ 30 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅቱን አጠናቆ ተማሪዎቹን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል ብለዋል።
የራያ ዩኒቨርሲቲ አዳሪ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር መምህር ግርማይ አብርሃ (ረዳት ፕሮፌሰር) እንደገለፁት ራያ ዩኒቨርሲቲ ብቃት ያላቸው ሃገር ወዳድ ተማሪዎችን ለማፍራት በማለም በ2016 ዓ/ም 8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ተፈትነው ከፍተኛ ውጤት ያመጡ የትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ሠላሳ (30) ተማሪዎች በ2017 ዓ/ም ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመጀመርያ ጊዜ ያስተምራል በማለት ሀሳባቸውን ገልፀዋል።
በተያያዘ ዜና የራያ ዩኒቨርሲቲ የቤተ ሙከራ እና ሰርቶ ማሳያ ዳይሬክተር መ/ር ህንፃ ገብረጊዮርጊስ (ረዳት ፕሮፌሰር) በበኩላቸው ራያ ዩኒቨርሲቲ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሒሳብ (STEM) ትኩረት አድርጎ በጋርዮሽ ሳይንስ መርሃ ግብር (Science Shared Program) ከ 2011 ዓ/ም ጀምሮ ከ9ኛ ክፍል ተማሪዎችን በብቃት እያስተማረ ይገኛል ብለዋል። መምህር ህንፃ አክለው ባስተላለፉት መልእክት ራያ ዩኒቨርሲቲ ከ2011 ዓ/ም ጀምሮ ከ9ኛ – 12ኛ ክፍል ያስተማራቸው 14 ተማሪዎች በ2016 ዓ/ም ሃገራዊ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው 13ቱም (92.86%) ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ በማምጣታቸው ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበ ሲሆን በቀጣይ ዓመትም ዩኒቨርሲቲው ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በመጨረሻም ይህ የመግቢያ ፈተና በተሳካ መንገድ እንዲከናወን የላቀ አስተዋፅእ ላበረከቱት የተለያዩ አካላት ዩኒቨርሲቲው ላቅ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል።
***********************************************
ራያ ዩኒቨርሲቲ
መስከረም 07/2017 ዓ/ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
***********************************************