ራያ ዩኒቨርሲቲ እና ትግራይ ኢንደስትሪ ቢሮ በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን የጋራ መግባቢያ ሰነድ (MoU) ዛሬ መስከረም 11/2017 ዓ/ም በመኾኒ ከተማ ተፈራረሙ።
የስምምነቱ ዋና ዓላማ ራያ ዩኒቨርሲቲ ከኢንደስትሪዎች ያለውን ትስስር በማጠናከር የሥራ ፈጠራ እንዲስፋፋ እና ማህበረሰብ አቀፍ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲስፋፋ በትብብር ለመስራት ነው።
ስምምነቱ የተፈረመው በራያ ዩኒቨርሲቲ ፕረዚደንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ የተመራ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራንና ተማራማሪዎች እና በትግራይ ኢንደስትሪ ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ገ/ሂወት ዓገባ የተመራ የቢሮው ሰራተኞች በመኾኒ ከተማ ባደረጉት የጋራ ውይይት ነው።
የራያ ዩኒቨርሲቲ ፕረዚደንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ በመክፈቻ ንግግራቸው ዩኒቨርሲቲያችን ከተለያዩ ኢንደስትሪዎች በማቀናጀት ምርምርና ኢንደስትሪ አስተሳስረን የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት፣ ውጤታማ የዓቅም ግንባታ ሥራ እንዲሰራና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር ከትግራይ ኢንደስትሪ ቢሮ ጋር ተባብረን እንሰራለን ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክተር መ/ር ደባሲ ግደይ፤ የከፍተኛ ትምህርት፣ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ ምርምር ተቋማት እና የኢንደስትሪ ትስስር አዋጅና ራያ ዩኒቨርሲቲ ከትግራይ ኢንደስትሪ ቢሮ ጋር ስለሚፈራረመው የመግባብያ ስምምነት ይዘት መሰረት በማድረግ ባቀረቡት የመወያያ ሐሳብ በትስስር አዋጁ ላይ የተካተቱ ቁልፍ ነጥቦች፣ ሃገራዊ፣ ክልላዊና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስር አደረጃጀት፣ ተግባርና ሀላፊነት እንዲሁም ዳይሬክቶሬቱ በዚህ ዓመት ያቀዳቸው አንኳር ነጥቦች በዝርዝር አቅርበዋል።
የትግራይ ኢንደስትሪ ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ገ/ሂወት ዓገባ በበኩላቸው የትግራይ ኢንደስትሪ ቢሮ በሚያስተዳድራቸው ትናንሽ፣ መካከለኛ እና ትላልቅ ኢንደስትሪዎች በጥናትና ምርምር የዳበሩና ማህበረሰብ አቀፍ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከራያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር እንሰራለን ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የተለያዩ ሀሳብ አስተያየቶች አንስተው በፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ፣ ዶ/ር ገ/ሂወት ዓገባ እና በሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራርያ ተሰጥቷል።
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ መስከረም 11/2017 ዓ/ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
****************************************