ራያ ዩኒቨርሲቲ ከትምህርት ሚኒስቴር በቁልፍ የአፈጻጸም አመላካቾች (Key Performance Indicators) ስምምነት ተፈራረመ

በትምህርት ሚኒስቴርና በሁሉም የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል ዛሬ ታህሳስ 16/2017 ዓ.ም የተፈረመው ቁልፍ የአፈጻጸም አመላካቾች (Key Performance Indicators) ስምምነት ራያ ዩኒቨርሲቲን በመወከል ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ስምምነቱን የፈረሙት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ንግድ እና ቀጠናዎች ትሥሥር ሚኒስቴር እና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የተከበሩ ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ እና የዩኒቨርሲቲው ጥረዚደንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ ሲሆኑ ስምምነቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ ብቃትና ችሎታ ያላቸው ምሩቃንን በማፍራት ሂደት ውስጥ ተጠያቂነትን ከማስፈን ባለፈ ውጤታማነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው፡፡
ቁልፍ የአፈጻጸም አመላካቾቹ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ ስራን በውጤት መምራት ወደሚያችል ስርዓት ማስገባት በሙያዊና ክህሎታዊ ስራዎች እንዲሁም በልህቀት ላይ በማተኮር የአገሪቱን ችግሮች መፍታት የሚችሉ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማድረግ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚን የማልማት ስራ ላይ የበኩላቸውን ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ የሚያስችሉ ናቸው፡፡
በስምምነቱ ፊርማ ስነ ስርዓት እንደተገለጸው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግልጽነትና ተጠያቂነትን ያሰፈነ አመራር እንዲከተሉ፣ አገሪቱ ለምታወጣው ሀብት ተመጣጣኝ ውጤት እንዲያስገኙ የአፈጻጸም አቅማቸው እንዲገመገምና ለስኬቱም እውቅና እና ሽልማት እንዲያገኙ ያግዛል፡፡

ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ታህሳስ 16 /2017 ዓ.ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
****************************************