ይህ የተገለፀው የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊና የራያ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ዶ/ር እያሱ አብርሃ፣ የደቡባዊ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የራያ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ሃፍቱ ኪሮስ፣ የደቡባዊ ትግራይ ዞን አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የእንዳ መኾኒ፣ ኦፍላ እና እምባ አላጀ ወረዳ ግብርና ባለሙያዎች፣ የአላማጣና መኾኒ ግብርና ምርምር ማእከላት ባለሙያዎች፣ የማይጨው ግብርና ኮሌጅ ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች፣ የዘር ብዜት ማህበራት፣ አርሶአደሮች፣ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ መምህራን እና ተማራማሪዎች፣ የትግራይ ባዮቴክኖሎጂ ማእክል ባለሙያዎች ዛሬ ጥቅምት 02/2017 ዓ/ም በራያ ዩኒቨርሲቲ የተከናወኑ የግብርና እና የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራዎች የመስክ ምልከታ ባደረጉበት ወቅት ነው።
በመስክ ምልከታው የተገኙት የራያ ዩኒቨርሲቲ ፕረዚደንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ ለእንግዶቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ካስተላለለፉ በኃላ ራያ ዩኒቨርሲቲ ከጦርነቱ በኃላ ቶሎ ወደ ስራ ገብቶ በመማር ማስተማር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ምርምር፣ ማህበረሰብ ጉድኝት፣ አስተዳደር፣ መሰረተ ልማት ግንባታ፣ ፅዱና አረንጓዴ ግቢ የመፍጠር ዘመቻ ውጤታማ ስራ በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።
ፕሮፌሰር ታደሰ አክለው እንደተናገሩት በዛሬው ዕለት ዩኒቨርሲቲው ከ Kansas State University እና CulivAid ጋር በመተባበር የሰራቸው የግብርና ምርምር ውጤቶች ለመገምገም እና ወደ ማህበረሰቡ ለማስፋፋት ዓቅም የገነባንበት እና ከአጋር አካላት ጋር ተቀናጅተን የሰራነውን ውጤታማ የግብርና ስራችንን ለማየት የበቃንበት ቀን በመሆኑ እንኳን ደስ አላን፤ አላችሁ ብለዋል።
ዶ/ር እያሱ አብርሃ ባደረጉት ንግግር በትግራይ ክልል ከጦርነቱ በፊት የነበረው የማምረት አቅም በጦርነቱ ምክንያት በጣም የቀነሰ ቢሆንም ከጦርነቱ በኃላ ግን በምግብ ራሳችንን ለመቻል፣ አርሶ አደሩ የተመጣጠነ ምርት እንዲያመርት፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ለማስፋፋት፣ ተማሪዎች የተግባር ትምህርት እንዲያገኙ እና መምህራን እውቀታቸው እንዲተገብሩ እንዲሁም ራያ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ልህቀት እና ማእከል ለማድረግ እያደረግን ላለነውን ጥረት የራያ ዩኒቨርሲቲ ለሌሎች አርአያ የሚሆን የግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ውጤታማ ስራዎችን በማከናወኑ ወሳኝ እና ሊመሰገን ይገባል በማለት ዘንድሮ ባለው ጥሩ ምርት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ፤ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ወደ ጥቅም ለመቀየር እና እየታየ ያለው የአንበጣ መንጋ ለመከላከል በቅንጅት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በራያ ዩኒቨርሲቲ ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ የስነ እፅዋት (Horticulture) ትምህርት ክፍል ተማራማሪ እና መ/ርት የሆኑት አስመረት ኪዳነ ራያ ዩኒቨርሲቲ በ 22 ሄክታር የምርምር ማሳ ላይ እያመረተ ያለው “ቦሩ” የተሰኘ የስንዴ ዝርያ ምርጥ ዘር ብዜት ሂደት፣ ጠቀሜታ እና የምርት መጠን ለጎብኚዎች ሙያዊ ማብራሪያቸውን ሰጥተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የስነ አዝርእት (Plat Science) ትምህርት ክፍል ተማራማሪ እና መ/ር መረሳ ሹሙየ በበኩላቸው ራያ ዩኒቨርሲቲ ከ Kansas State University ጋር በመተባበር ድርቅ እና በሽታዎች የሚቋቋሙ እና የተሻለ ምርት የሚሰጡ፣ የማህበረሰብ ተደራሽነት የሚያረጋግጡ የቦቆሎ፣ ስንዴ እና ባቄላ ዝርያዎች በሰርቶ ማሳያ ቦታ ላይ እየተሰሩ ያሉ የምርምር ክንውኖች እና የማዳበርያ አጠቃቀም ገለፃ አድርገዋል።
በሌላ በኩል የአትክልት ምርት ለማዘመን እና ለማሳደግ አዳዲስና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም Cauliflower , Broccoli, cabbage የተሰኙ አዳዲስ ዝርያዎች ወደ ማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ራያ ዩኒቨርሲቲ ከ CultivAid ጋር በመተባበር በትኩረት እየሰራ ይገኛል ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ግብርና እና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ዲን መ/ር ሞገስ አሰፋ ናቸው።
በራያ ዩኒቨርሲቲ የስነ እፅዋት (Horticulture) ትምህርት ክፍል ሃላፊ እና ተማራማሪ የሆኑት መ/ር ተስፋይ ተ/ሃይማኖት ራያ ዩኒቨርሲቲ ከ Kansas State University እና ትግራይ ባዮቴክኖሎጂ ተቋም ጋር በመተባበር የማህበረሰቡ ችግር የሚፈቱ፣ አስቸጋሪ የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋሙ እና የተሻለ ምርት የሚሰጡ እንደ ቀይ እና ነጭ ሽንኩርት፣ ድንች እና ጥቅል ጎመን የመሳሰሉ የአትክልት ዝርያዎች የምርምር እና ብዜት ስራዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እና የከተማ እርሻ ለማዘመን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
ከመስክ ምልከታ ተሳታፊዎች ጋር በተደረገ ውይይት በተሳታፊዎች የተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች በሚመለከታቸው ባለሙያዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አበራ ከደነው ለተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልእክት ራያ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው ዘርፍ የሰራው ውጤታማ ስራ ለማስቀጠል፣ የግብርና ምርት እና ምርታማነት ለማሳደግ የማህበረሰቡ ተደራሽነት ለማሳደግ፣ የዘር እጥረት ለመቅረፍ፣ የመህበረሰብ ችግር ለመፍታት ከሚመለከታቻው አካላት ጋር በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል።
በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕረዚደንት ዶ/ር ነጋ ዓፈራ ለተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልእክት ራያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰባችን ችግር ለመፍታት፣ የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት፣ የዘር አቅርቦት ለመቅረፍ እና ማህበረሰብ ተኮር የምርምር ስራዎች በመስራት ውጤታማ የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎች በቀጣይነት አጠናክረን እንሰራለን ብለዋል።
******************************************
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ጥቅምት 02/2017 ዓ/ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
*******************************************