በመንገድ ትራፊክ ደኅንነት” ዙርያ በተለያየ ደረጃ ከሚገኙ የደቡባዊ ትግራይ ዞን ፖሊስ ትራፊክ አባላት ጋር የምክክር መድረክ መርኃ ግብር ተካሄደ

የራያ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሠብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት እና የኢንጅነሪንግ እና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ከደቡባዊ ትግራይ ዞን ፖሊስ ትራፊክ መምሪያ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በተለያየ ደረጃ ከሚገኙ የደቡባዊ ትግራይ ዞን ፖሊስ ትራፊክ አባላት ጋር “በመንገድ ትራፊክ ደኅንነት” ዙርያ የካቲት 16 /2017 ዓ/ም የምክክር መድረክ መርኃ ግብር ተካሄደ።
መርኃ ግብሩ በመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር ባለድርሻ አካላት አደጋውን ለመቀነስ የሚያደርጉትን ጥረትና ተሳትፎ ለማጠናከር እና አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ነው።የራያ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማኅበረሠብ ጉድኝት ምክትል ፕረዚደንት ልዩ ረዳት መሐመድአወል የሱፍ (ዶ/ር) በንግግራቸው ራያ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር፣ ምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎች በተጨማሪ በማኅበረሠብ አገልግሎት ዘርፍ የማኅበረሠቡ ችግር ለመፍታት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ መምጣቱን በመግለጽ ከነዚህ አንዱ በዓለማችን በሰው ህይወት እና ንብረት ብሎም በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ ስነ-ልቦናዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ትልቅ ጉዳት እያስከተለ ያለው አስከፊውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ እና የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ለማረጋገጥ ወሳኝ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርኃ ግብር ተዘጋጅቷል ብለዋል።
የራያ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሠብ ጉድኝት ዳይሬክተር መምህር ደባሲ ግደይ በበኩላቸው የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ለማረጋገጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና፣ የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት፣ ማስፈፀሚያ ምሶሶዎች፣ ቁልፍ ችግሮች፣ ስትራቴጂክ ጉዳዮች፣ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ፣ አገራዊ እና ክልላዊ የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት እና አደጋ አሁናዊ ገጽታ፣ ለመንገድ ትራፊክ አደጋ መከሰት ምክንያቶችና ውጤቶች እንዲሁም አደጋውን ልዩ የሚያደርገው እና የአደጋውን አስከፊነት ለመቀነስ ምን መደረግ እንዳለበት ገለጻ አድርገዋል።
መምህር ደባሲ በገለጻቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ለማረጋገጥ እና የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ ማህበራዊ ኃላፊነታቸው ማከናወን፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዎችን በመስጠት ግንዛቤ መፍጠር፣ በተማሪዎች ዘንድ አዎንታዊ ተጽዕኖ መፍጠር፣ ምርምር ማካሄድ፣ የትራፊክ ዘይቤዎችን በመተንተን እና የአካባቢ ችግሮችን መፍታት፣ አካታች ስርዓተ ትምህርት መተግበር እና ልዩ ልዩ ዓውደ ጥናቶችን በማካሄድ ውጤታማ ሥራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
የራያ ዩኒቨርሲቲ የኢንጂነሪንግ እና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ዲን መምህር ታደሰ ተክሌ የአውቶሞቲቭ እና ትራፊክ ደኅንነት መሠረታዊ ጽንሰ ሀሳብ እና ዓላማ፣ የሥራ ቦታ ደኅንነት፣ የአደጋ ምንነትና መንሥኤዎች፣ የትራፊክ እና ፖሊስ ትራፊክ ምንነት፣ የፖሊስ ትራፊክ ኃላፊነት፣ ፖሊስ ትራፊክ መርኆች፣ ማኅበረሰብ ከፖሊስ ትራፊክ፣ ሹፌሮች ከፖሊስ ትራፊክ፣ ፖሊስ ትራፊክ ከመንግስት ምን እንደሚጠብቁ እንዲሁም ፖሊስ ትራፊክ በዕውቀት እና ክህሎት ብቁ በመሆን እና ሊሰሯቸው የሚችሉ ስህተቶች በማስወገድ ማኅበረሠባቸውን እንዴት ማገልገል እንደሚችሉ ዝርዝር ሙያዊ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው በኢንጂነሪንግ እና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ሥር የአውቶሞቲቭ ትምኅርት ክፍል ኃላፊ መምህር አታኽልቲ ዳዊት፤ የተሽከርካሪዎች ምርመራ ምንነት፣ ዓላማ፣ አሥፈላጊነት፣ የምዝገባ ዓይነቶች፣ ለአዲስ ተሽከርካሪዎች ምዝገባ የሚያስፈልጉ ሰነዶች፣ የተሽከርካሪ ዓይነቶች እና ምርመራ መስፈርቶች እንዲሁም የትራፊክ አደጋ ምርመራ ምንነት፣ ዓይነቶች፣ መንስኤዎች፣ ሂደቶች እና ደረጃዎች ሙያዊ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በመርኃ ግብሩ የደቡባዊ ትግራይ ዞን ፖሊስ ትራፊክ መምሪያ ኃላፊ ኢንስፔክተር ሽሻይ ገ/ማርያም ዙርያ የትግራይ ክልል መመሪያን መሰረት በማድረግ የትራፊክ አደጋ ምርመራ ምንነት፣ ሂደት፣ ትግበራ እና ሪፖርት አቀራረብ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
በመርኃ ግብሩ ከተሳታፊዎች ጋር በተደረገ ውይይት ራያ ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ለጋራ ትውውቅ፣ ያለባቸውን የዓቅም ውሱንነት ለመፍታ እና የሥራ ተነሳሽነት የሚያዳብር መርኃ መሆኑን ተሳታፊዎች አመስግነው ለቀጣይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጀተን በመሥራት ከአደጋ የጸዳ አከባቢ ለመፍጠር እንሰራለን ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የራያ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ አባል እና የደቡባዊ ትግራይ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አቶ ሃፍቱ ኪሮስ ባደረጉት ንግግር ብዙ ችግሮች ተቋቁመው እየሰሩ በዞኑ ለሚገኙ ፖሊስ ትራፊኮች እና የምክክር መድረኩን ላዘጋጀው ራያ ዩኒቨርሲቲ አመስግነው የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ለማረጋገጥ እና የትራፊክ አደጋዎች ለመቀነስ ቀጣይነት ያለው ጠንካራ ስራ መሰራት ያስፈልጋል ብለዋል
********//*****************************
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ የካቲት 17/ 2017 ዓ.ም
ዕውቀት ለማኅበረሠባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አሥፈጻሚ
*******//******************************