ወቅታዊ የምግብ ዋጋ ንረትን መነሻ በማድረግ ትምህርት ሚኒስቴር ባደረገው ጥናት መሰረት ከመጪው ታህሳስ 1 ቀን 2017 ጀምሮ መመሪያው የሚተገበር የከፍትኛ ትምህርት ተቋማት የምግብ በጀት በቀን ወደ 100 ብር ከፍ እንዲል እና በተቋማቱ የምግብ ሜኑ ተመሳሳይ እንዲሆን መወሰኑን ተከትሎ ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በምግብ በጀት ተመን ማሻሻያ ዙርያ ዛሬ ዓርብ ታህሳስ 04 ቀን 2017 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር ተካሄደ።
የራያ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር እና ልማት ምክትል ፕረዚደንት ዶ/ር ክብሮም ካሕሱ ለተማሪዎች እንደገለፁት የምግብ በጀት ተመን ማሻሻያው የሁሉም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተደጋጋሚ ጥያቄ እንደነበር አስታውሰው ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን ለቀን በ22 ብር መመገብ በጣም ከባድ እንደነበር እና ራያ ዩኒቨርሲቲ ግን የተለያዩ አማራጮች ይጠቀም ነበር ብለዋል።
ዶ/ር ክብሮም አክለው እንደገለፁት፤ አዲስ በፀደቀው የምግብ በጀት ተመን ማሻሻያ መሰረት ዩኒቨርሲቲያችን አስፈላጊውን ግብአት በማሟላት እና አገልግሎት በመስጠት ተማሪዎቹን ትኩረታቸው በመማር እና ማስተማር እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።
የተማሪዎች አገልግሎት ዲን መምህር ረዳኢ ስብሃቱ በበኩላቸው በተደረገው የተማሪዎች የምግብ በጀት ተመን ማሻሻያ የተማሪዎች መብትና ግዴታ እንዲሁም ያሉት እድሎች እና ስጋቶች ማብራሪያ በመስጠት በአዲሱ የበጀት ተመን መሰረት ዩኒቨርስያችን ባለን የተማሪ ቁጥር ልክ ገንዘቡ እንደሚለቀቅ አውስተዋል።
በተደረገው የተማሪዎች የምግብ በጀት ተመን ማሻሻያ ዙርያ ከተማሪዎች የተለያዩ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን ዶ/ር ክብሮም ካሕሱ እና መምህር ረዳኢ ስብሃቱ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎች የሚቀርብ ምግብ በዐይነት፣ መጠን እና ጥራት ለማሻሻል በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ታህሳስ 04 ቀን 2017 ዓ/ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
*****************************************