በክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም የሚመራ የልኡክ ቡድን አባላት በዩኒቨርሲቲው እየተሰሩ ያሉ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ጉብኝት አድርገዋል።

በራያ ዩኒቨርሲቲ በ2016 ዓ/ም በ900 ሚልየን ብር በጀት እየተሰሩ ያሉ የመንገድ እና ፍሳሽ ማስወገጃ፣ ውሃ እና መብራት ዝርጋታ፣ የአጥር ግንባታ፣ የተማሪዎች መማርያ፣ መኝታና የልብስ ማጠብያ ህንፃዎች፣ የተማሪዎች የኤሌክትሪክ ምግብ መስሪያ፣ የስብሰባ እና የተማሪዎች መመገብያ የያዘ ዘመናዊ አዳራሽ እና እንዲሁም ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች በክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም የሚመራ የልኡክ ቡድን አባላት ዛሬ ሚያዝያ 19/2016 ዓ/ም ጎብኝተዋል።
በመስክ ምልከታው የዩኒቨርሲቲው ፕረዚደንት ታደሰ ደጀኔ (ፕሮፌሰር)፣ አስተዳደር እና ልማት ምክትል ፕረዚደንት ክብሮም ካሕሱ (ዶ/ር)፣ የደቡባዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ሃፍቱ ኪሮስ፣ የትግራይ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ከላሊ አድሀና፣ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣ የትግራይ ደቡባዊ ዞን ማህበረሰብ ተወካዮች፣ ሀገር ሽማግሌዎች፣ ሃይማኖት መሪዎች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች እና ሚድያ አካላት ተገኝተዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሮጀክት ግንባታ ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ይትባረክ ትኩእ ለልኡክ ቡድኑ አባላት በሰጡት ማብራርያ ከማይጨው 01 ቀበሌ አሰፋልት መታጠፍያ እስከ ዩኒቨርሲቲው በር እየተሰራ ያለው ዘመናዊ የአስፋልት መንገድ እና የፍሳሽ ማስወገጃ ስራ 75% መጠናቀቁን እና ሁሉም ፕሮጀክቶች ሰኔ 2016 ዓ/ም ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ይደረጋሉ ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና ልማት ምክትል ፕረዚደንት ዶ/ር ክብሮም ካሕሱ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው እየተሰሩ ያሉ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች በዲጂታላይዜሽን፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ ግቢ ውበት እና ለማህበረሰቡ ጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተው ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ተጠናቀው ይመረቃሉ ብለዋል።
ዶ/ር ክብሮም ካሕሱ በተጨማሪ ለእንግዶቹ እንደተናገሩት ይህ የተሳካ ስራ እንዲሰራ የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ፣ የዩኒቨርሲቲው አመራር እና የሚመለከታቸው አካላት ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አመስግነው በዩኒቨርሲቲው የተቋቋመ የፕሮጀክቶቹ ጥራት ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ሁልጊዜ ዓርብ በመጎብኘት ጥራቱን በመከታተል ገንቢ አስተያየቱን እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።