በዩኒቨርሲቲው ለተከታታይ 5 ቀናት ሲሰጥ የቆየው የአሰልጣኞች ስልጠና ተጠናቀቀ።

በራያ ዩኒቨርሲቲ ከመስከረም 20 እስከ 24/2017 ዓ/ም ለተከታታይ 5 ቀናት ለአመራሮችና መምህራን ሲሰጥ የቆየው የአመራር ብቃትና የመማር ማስተማር ሳይንሳዊ ክህሎት የአሰልጣኞች ስልጠና ተጠናቀቀ።
በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የራያ ዩኒቨርሲቲ ፕረዚደንት ታደሰ ደጀኔ (ፕሮፌሰር) ዩኒቨርሲቲው እያስመዘገባቸው ያለ ዘርፈ ብዙ ውጤታማ ስራዎች ለማስቀጠል የሰራተኞቻችን ሁለንተናዊ ዓቅም ገንብተን ለበለጠ ውጤት እንነሳለን ብለዋል።
ስልጠናውን የሰጡት የራያ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ም/ሰብሳቢ እንዲሁም የአካዳሚክና ምርምር ተጠሪ ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ እና የቀድሞ የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ፕረዚደንት ዶ/ር አልማዝ ባራኪ ሲሆኑ የአመራር ክህሎትና ብቃት ለማሳደግ የለውጥ አስተዳደር፣ የአመራር ክህሎት፣ ተቋማዊ ለውጥና ዓቅም ግንባታ፣ የህዝብ ጉዳዮችን መምራት እና ማስተዳደር፣ በባህሎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች እና የግጭት አፈታት ዘዴዎች፣ የራሳችን ምስል፣ የመሪዎች ሚና፣ ከራሳችን መማር፣ የቴክኖሎጂ ውህደትና የመገናኛ ዘዴዎች፣ በሰለጠነ ዓለም ውስጥ የሚፈጠር የባህል ለውጥ፣ ዓለም አቀፍ የግንኙነት አውታረ መረቦች፣ አዕምሮ እና አውታረ መረቦች በማደስ ዓለምን መለወጥ እንዲሁም የሪፖርት አፃፃፍ እና አቀራረብ የቡድን ውይይት እና ነፀብራቅ (Reflection) ተደርጓል።
በሌላ በኩል የህይወት ክህሎት ስልጠናው ደግሞ የዕውቀት አስተዳደር፣ የዳሰሳ ጥናት፣ የጊዜ አስተዳደር፣ ሚዛናዊ አስተሳሰብ፣ የግጭት አፈታት ሂደት፣ የቡድን ስራና ቅንጅት፣ የተግባቦት ክህሎት፣ የክፍል አስተዳደር፣ የምዘና አስተዳደር፣ ስሜታዊ ልህቀት፣ ስርዓተ ትምህርት እና ሙያዊ ስነ ምግባር የሚሉ የስልጠና አጀንዳዎች ትኩረት ያደረገ ነበር።
በስልጠናው ፕሮፌሰር መንገሻ እና ዶ/ር አልማዝ ሰልጣኞች ላሳዩት መልካም ስነ ምግባር እና ንቁ ተሳትፎ ያመሰገኑ ሲሆን ለሰልጣኞች የምስክር ወረቀት በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር እና ልማት ምክትል ፕረዚደንት ዶ/ር ክብሮም ካሕሱ ተሰጥተዋል።
ሰልጣኞችን በመወከል ሃሳባቸውን የሰጡት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ፕሮግራም ዳይሬክተር ቀሲስ ንጉስ መሰለ (ዶ/ር) ስልጠናው እጅግ ውጤታማ እንደነበርና አሰልጣኞች ካለንበት ድረስ በመምጣት ያካበቱትን ዕምቅ ዕውቀት ላካፈሉን እና ዕድሉን ለሰጠን ራያ ዩኒቨርስቲ እናመሰግናለን በማለት ያገኘነውን ዕውቀት እድሉን ላላገኙ በማካፈልና በሰለጠንበት ልክ ተግባራዊ ለውጥ ማምጣትና ያሉብንን ክፍተቶች መሙላት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲውን በመወከል የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት ዶ/ር ክብሮም ካሕሱ አሰልጣኞቹን አመስግነው ሰልጣኞች ባገኙት ትምህርት በየዘርፉ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት እና የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ መትጋት ይጠበቅባችኋል ብለዋል።
******************************
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ መስከረም 25/2017 ዓ/ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
************************************