የራያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር፣ ሕትመት፣ ስነ-ምግባር እና ኢንዳክሽን ዳይሬክቶሬት ያዘጋጀው የተመራማሪዎች (Principal Investigator) እና ተባባሪ ተመራማሪዎች (Co-Investigators) የምርምር ስነ-ምግባር (Research Ethics) እና የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት ስልጠና በሚመለከታቸው ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን ስልጠናው በዋናነት ተመራማሪዎቹ የምርምር መርህ ተከትለው ወቅታዊ፣ ውጤታማ እና የተሟላ ምርምር በመስራት አስፈላጊውን ሪፖርት በግልፅነት እና ታማኝነት ለሚለከተው አካል እንዲያስረክቡ ለማስቻል ያለመ ነበር፡፡
የራያ ዩኒቨርሲቲ ፕረዚደንት ታደሰ ደጀኔ (ፕሮፌሰር) ባቀረቡት ፅሁፍ መሰረት የምርምር ስነ-ምግባር (Research Ethics) ምንነት፣ ጠቀሜታ፣ ሂደት እና የሚሰሩ የምርምር ስራዎች የማህበረሰቡና ሃገሪቱን አሁናዊ ችግሮች የሚፈቱ መሆን እንዳለባቸው እና ምርምር ለምን እንደሚሰራ ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ አክለው እንደገለፁት የጥናትና ምርምር ውጤታማነት ለተገልጋዮች፣ ውስጥ ዓቅም ግንባታ፣ ማህበረሰብ፣ አጋር አካላት እና መልካም ገፅታ ግንባታ ያለውን ፋይዳ አብራርተዋል፡፡
በራያ ዩኒቨርሲቲ የፋይናንስ አስተዳደር የፋይናንስ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ብርሃኑ ረዳኢ፤ የፋይናንስ ኣዋጅ 648/2001፣ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት የሒሳብ አያያዝ ስርዓት፣ የፈደራል መንግስት የጥሬ ገንዘብ አስተዳደር መመርያ 3/2003 እና የፌደራል መንግስት የፋይናንስ ሃላፊነት መመርያ ቁጥር 6/2003 መሰረት አድርገው በስልጠና አከፋፈል መሟላት ያለባቸው፣ አበል አከፋፈል፣ በውል የሚሰሩ ስራዎች፣ የቀን (ኮንትራት) ሰራተኞች፣ ትራንስፖርት፣ የሆቴል መስተንግዶ፣ የመረጃ ሰብሳቢ፣ የመሬት እና መኪና ኪራይ፣ የላብራቶሪ ውጤት እና ጥቃቅን ግዢዎች ለተመራማሪዎች ሙያዊ ማብራሪያቸውን ሰጥተዋል፡፡
የራያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር፣ ሕትመት፣ ስነ-ምግባር እና ኢንዳክሽን ዳይሬክተር መ/ር ተመስገን ተስፋይ (ረ/ፕሮፌሰር) በበኩላቸው በጥናትና ምርምር ሂደት ዙርያ ተመራማሪዎች ሊያደርጓቸው የሚገቡ ቁልፍ ተግባራት፣ ሊገጥሟቸው የሚችሉ ተግዳሮቶች እና የመፍትሔ ሀሳቦች ለሰልጣኞች ሙያዊ ማብራሪያቸውን የሰጡ ሲሆን በሰልጣኞች የተነሱ ጥያቄዎች በሚመለከታቸው ባለሙያዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
**************************************
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ/ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
**************************************