በዩኒቨርሲቲው የ12ኛ ማህበራዊ ሳይንስ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተካሄደ ነው።

ራያ ዩኒቨርሲቲ በቀድሞው ሥርዓተ-ትምህርት የተማሩ በ2013 ዓ/ም እና በ2014 ዓ/ም የትምህርት ዘመን መፈተን የነበረባቸው የ12ኛ ክፍል የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኝ ተማሪዎች ከሰኔ 29-30/2016 ዓ/ም በደማቅ ስነ ስርዐት ተቀብሎ ሰኞ ሐምሌ 01/2016 ዓ/ም በሚመለከታቸው አካላት ለተፈታኝ ተማሪዎች ማብራሪያ (Orientation) በመስጠት ሐምሌ 02/2016 ዓ/ም ፈተናው ተጀምሯል።
ከዩኒቨርሲቲው ፈተና አስፈጻሚ ግብረ ሃይል በተገኘው መረጃ መሰረት በደቡባዊ እና ደቡብ ምስራቅ ትግራይ ከሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በትምህርት ሚኒስቴር የተመደቡ 2433 የ12ኛ ክፍል የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኝ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ፈተናውን እየወሰዱ እንደሚገኙ እና ተፈታኝ ተማሪዎች በተረጋጋ መንፈስ ትኩረታቸውን በፈተናው ላይ ብቻ እንዲያደርጉ እንዲሁም ጥሩ ውጤት እንዲያመጡ ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርጓል።
የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ባወጣው መረጃ መሰረት በ2012 ዓ/ም 10ኛ ክፍል የነበሩ (Code 01) ከ31,000 በላይ የማህበራዊ እና ተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ከሐምሌ 2-5/2016 ዓ/ም እንዲሁም በ2012 ዓ/ም 11ኛ ክፍል የነበሩ (Code 07) የማህበራዊ እና ተፈጥሮ ሳይንስ ከ23,000 በላይ ተማሪዎች ደግሞ ከሐምሌ 9-12/2016 ዓ/ም በመቐለ፣ አክሱም፣ ዓዲ ግራት እና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች ይፈተናሉ።
ዘንድሮ 701,489 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና እንደሚወስዱ የፌደራል የፈተና እና ምዘናዎች ኤጀንሲ አመላክቷል።
መልካም ዕድል ለተፈታኝ ተማሪዎች!
***********************************
ራያ ዩኒቨርሲቲ
ሐምሌ 04/2016 ዓ/ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
************************************