በጡት እና የማኅጸን በር ካንሰር ዙርያ ለዩኒቨርሲቲው ሴት መምህራን እና አስተዳደር ሰራተኞች ስልጠና ተሰጠ

የራያ ዩኒቨርሲቲ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ አካትቶ ትግበራ ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት ከህማብረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የጡት እና የማኅጸን በር ካንሰር ስልጠና ለዩኒቨርሲቲው ሴት መምህራን እና አስተዳር ሰራተኞች ታህሳስ 08 ቀን 2017 ዓ.ም ተሰጥቷል።
የስልጠናው ዋና ዓላማ የጡት እና ማኅጸን በር ካንሰር ግንዛቤን ለማስጨበጥ እና የቅድመ ምርመራ እና መከላከል አስፈላጊነትን ለማስተዋወቅ ነው።
በስልጠናው የዩኒቨርሲቲው አካ/ምር/ቴክ/ሽግ/ማህ/አገልግሎት ምክትል ፕረዚደንት ዶ/ር ነጋ ዓፈራ ባስተላለፉት መልእክት መሰረት በአሁኑ ሰዓት የጡት እና ማኅጸን በር ካንሰር በሴቶች ላይ ትልቅ የጤና ስጋት ስለሆነ ሴቶች ማህበረሰብን የሚወክሉ እና ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው በመሆናቸው እያንዳንዱ ሴት ስለ ህመሙ አደገኛ ሁኔታዎች እና የመከላከያ እርምጃዎችን አስቀድመው እንዲማሩ ወሳኝ መርሃ ግብር ስለሆነ በአግባቡ መከታተል ይኖርባችኋል ብለዋል።
ስልጠናውን የሰጡት የማይጨው ለምለም ካርል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር፣ የጽንስና ማኅጸን ስፔሻሊስት እና ከፍተኛ አማካሪ ዶ/ር አክሊል አለማየሁ ሲሆኑ የጡት እና የማኅጸን በር ካንሰር ምንነት፣ ዓይነቶች፣ መንስኤዎች፣ ምልክቶች፣ የተሳሳቱ ግንዛቤዎች፣ ስርጭት፣ የቅድመ ምርመራ እና የህክምና ሂደቶች እና ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች ዙርያ ዝርዝር ሙያዊ ገለፃ አድርገዋል።
እንደ ዶ/ር አክሊል ገለፃ የጡት እና ማኅጸን በር ካንሰር በሁሉም ሰው የሚፈራ ቢሆንም ቀደም ብሎ ከተገኘ ግን የሚድን እና ለህመሙ ተጋላጭ ከሚያደርጉ መንስኤዎች ራሳችሁን በመጠበቅ እና አስቀድሞ በማወቅ እንዲሁም ውጤታማ የመከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀም ህይወትን ማዳን ይችላል ብለዋል፡፡
የBGI Ethiopia ራያ ቢራ ፋብሪካ የህክምና ክፍል ሃላፊ የህኑት አቶ ያሬድ ደሞዝ በበኩላቸው የጡት እና የማኅጸን በር ካንሰር ስርጭት በBGI Ethiopia የተካሄደ የዳሰሳ ጥናት ውጤት እና የጡት እና የማኅጸን በር ካንሰር የሚያስከትሉት ቁጠባዊ፣ ማህበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ተፅእኖዎች እንዲሁም ተቋሙ የዳሰሳ ጥናቱ ውጤት መሰረት በማድረግ ተከታታይ የስልጠና፣ የክትትል እና ድጋፍ መርሃ ግብር መዘጋጀቱን በመግለፅ ይህ ተግባር በሁሉም ተቋማት ሊለመድ የሚገባው ተቋማዊ ልምድ ነው ብለዋል።
በስልጠናው የተሳተፉት ሰራተኞች ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀላቸውን ስልጠና እጅግ ጠቃሚ እና ስለ ጡት እና ማኅጸን በር ካንሰር በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ከስልጠናው ተሳታፊዎች ጋር በተደረገ ውይይት በተሳታፊዎች በዙርያው ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች በባለሙያዎቹ ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ታህሳስ 08 ቀን 2017 ዓ.ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
****************************************