ተማሪዎች ባስመዘገቡት ውጤት ሳይዘናጉ ቀጣይነት ያለው የትምህርት ብቃት ማንፀባረቅ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ለማበረታታት እና በተማሪዎቹ ዘንድ ውጤታማ የትምህርት ፉክክር ለመፍጠር እና ይህን ውጤት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በ2017 የትምህርት ዘመን 1ኛ ወሰነ ትምህርት ከየትምህርት ክፍሉ ከፍተኛ የትምህርት አፈፃፀም እና ብቃት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የሽልማት እና እውቅና መርሃ ግብር መጋቢት 20/2017 ዓ.ም ተካሄደ።
በመርሃ ግብሩ ተገኝተው ለተሸላሚ ተማሪዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ያስተላለፉት የዩኒቨርሲቲው ፕረዚደንት ተወካይ ዶ/ር ነጋ ዓፈራ ተማሪዎች ባስመዘገባችሁት ውጤት ሳትዘናጉ ቀጣይነት ያለው የትምህርት ብቃት ማንፀባረቅ ይጠበቅባቹኃል በማለት የሽልማት እና እውቅና መርሃ ግብሩ በየሰሚስተሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የራያ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ እና ማሻሻያ ዳይሬክተር መምህር ብርሃነ ጸጋይ (ረዳት ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ በመማር ማስተማር ዘርፍ በተማሪዎች እየታዩ ያሉ ክፍተቶች እና መፍትሔዎቻቸው ዝርዝር ገለጻ አድርገዋል።
በዩኒቨርሲቲው በ2017 የትምህርት ዘመን 1ኛ ወሰነ ትምህርት ከየትምህርት ክፍሉ ከፍተኛ የትምህርት አፈፃፀም እና ብቃት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ይሄንን ውጤት አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት ከአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕረዚደንት ዶ/ር ነጋ ዓፈራ እጅ የገንዘብ እና ምስክር ወረቀት ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገልግሎት ዲን መምህር ረዳኢ ስብሃቱ በመዝጊያ ንግግራቸው እንደተናገሩት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ቆይታችሁ ውጤታማ ለመሆን የዩኒቨርሲቲው ህግ እና ደምብ በአግባቡ መተግበር ይኖርባቹኃል ብለዋል።
ተማሪዎች ከሽልማቱ ስነ ስርዓት በኃላ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ባዘጋጀላቸው የእውቅና እና ሽልማት መርሃ ግብር ተነሳስተው ውጤቱን ለማጠናከር እንደሚተጉ ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ የተማሪዎች የኪነት ቡድን አባላት የተለያዩ ሙዚቃዎች፣ ውዝዋዜዎች፣ ግጥም፣ ልዩ ተሰጥዖ እና የባህል ትርኢቶች አቅርበዋል።
****************************************
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ መጋቢት 20/ 2017 ዓ.ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
****************************************