በሃገር አቀፍ ደረጃ ከጥር 26 – 30/ 2017 ዓ.ም ለአምስት ተከታታይ ቀናት በራያ ዩኒቨርሲቲ ሲሰጥ የቆየው የ2017 ዓ.ም አጋማሽ የቅድመ ምረቃ የተማሪዎች መውጫ ፈተና (Exit Exam) ዛሬ ጥር 30/ 2017 ዓ.ም በስኬት መጠናቀቁን የፈተናው አሥፈጻሚ ግብረ ኃይል ገልጿል።
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማኅበረሠብ አገልግሎት ምክትል ፕረዚደንት እና የፈተናው ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ነጋ ዓፈራ (ዶ/ር) የመውጫ ፈተናውን መጠናቀቅ አስመልክተው ለዩኒቨርሲቲው የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አሥፈጻሚ ጽ/ቤት በሰጡት አስተያየት፤ ራያ ዩኒቨርሲቲ ለፈተናው አስፈላጊውን ግብኣት በማሟላት እና በቂ የቅድመ ዝግጅት ስራዎቹን በማከናወን ከጥር 8-14/ 2017 ዓ.ም ተፈታኞች እንዲመዘገቡ በማመቻቸት ፈተናው ከጥር 26 – 30/ 2017 ዓ.ም በተሳካ መንገድ እንዲሰጥ በየጊዜው ክትትል እና ድጋፍ መደረጉን ገልጸው ፈተናው በተሳካ መንገድ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ዶ/ር ነጋ አክለው ባስተላለፉት የምስጋና መልእክት ለተከታታይ 5 ቀናት ከጥዋቱ 12:30 እስከ ምሽቱ 1:00 በፈተና ማእከል በማሳለፍ በትጋት በቅንነትና በፍፁም ታማኝነት ኃላፊነታችሁን የተወጣችሁ የመውጫ ፈተና አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት፣ ፈታኝ መምህራን፣ የICT ባለሙያዎችና ፀጥታ አካላት እንደ አንድ ቤተሰብ በመተሳሰብና በመናበብ የተሰጣችሁ ተቋማዊ ኃላፊነት በተገቢው በማጠናቀቃችሁ በዩኒቨርሲቲው ማናጅመንት ስም ምስጋናቸውን አሥተላልፈዋል።
ከትምህርት ሚኒስቴር ለሱፐርቪዝን የመጣችው እህታችን ለምለም ደምሴ ፈተናው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ላደረገችው በጎ አስተዋፅኦ ዩኒቨርሲቲው ታላቅ ምስጋናውን ያቀረበ ሲሆን መልካም ጉዞ እንዲሆንልሽ ምኞታችን ነው።