ይህ የተገለጸው በራያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር፣ ሕትመት፣ ሥነ ምግባር እና ሥርፀት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት በጭብጥ የምርምር ንድፈ ሃሳብ አጻጻፍ (Thematic Research Proposal Writing) ዙርያ ለዩኒቨርሲቲው ሴት መምህራን እና ተመራማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከታኅሣሥ 25-26/ 2017 ዓ.ም በመኾኒ ከተማ በተሰጠበት ወቅት ነው።
የሥልጠናው ቁልፍ ዓላማ በዩኒቨርሲቲው የሚደረጉ የተለያዩ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮች የሴት መምህራን እና ተመራማሪዎች ዓቅም ለማሳደግ እና ውጤታማ አሥተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ነው።
ሥልጠናው መንግስት ቁልፍ የዕድገት እና የምርምር አጀንዳዎች መሰረት በማድረግ ባስቀመጣቸው አምስት የምርምር አጀንዳዎች በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በቴክኖሎጂ፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በማዕድን እንዲሁም ሁለ ገብ ጭብጥ የምርምር አጀንዳዎች ጤና፣ ትምህርት፣ አሥተዳደር፣ ሰብኣዊ ደኅንነት እና ቀጠናዊ ትስስር ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነበር።
የራያ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማኅበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕረዚደንት ልዩ ረዳት መሐመድአወል የሱፍ (ዶ/ር) በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር በጭብጥ የምርምር አጀንዳዎች (Thematic Research Areas) ዙርያ የተቀመጡ አቅጣጫዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የጭብጥ የምርምር አጀንዳዎች (Thematic Research Areas) ምንነት፣ ባህሪያት፣ አስፈላጊነት፣ አተገባበር፣ ይዘት፣ ሂደት፣ የምርምር ንድፈ ሃሳብ አጻጻፍ እንዲሁም የራያ ዩኒቨርሲቲ ጭብጥ የምርምር አጀንዳዎች እና ሃገራዊ የምርምር ስትራቴጂ ማዕቀፍን በተመለከተ ሥልጠና የሠጡት ደግሞ መምህር ኤልሳ ገብረጊዮርጊስ እና ዶ/ር ገብረመድህን ጎዲፍ ናቸው።
ከሠልጣኝ መምህራን ጋር በተደረገ ውይይት ለተነሱ የተለያዩ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እና ማብራሪያ ተሠጥቷል።
ከዚህ በፊት ዳይሬክቶሬቱ ለመምህራን እና ተመራማሪዎች የተለያዩ የዓቅም ግንባታ ስልጠናዎች መስጠቱን የሚታወስ ነው።
በመጨረሻም ለአሠልጣኞች እና ሠልጣኝ መምህራን የምስክር ወረቀት ተሠጥቷል።
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ታኅሣሥ 26/ 2017 ዓ.ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ
*******************************************