የራያ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ነጻ የሕግ ድጋፍ ማእከል በድምቀት ተመርቋል

የራያ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ነጻ የሕግ ድጋፍ ማእከል የራያ ዩኒቨርሲቲ ፕረዚደንት ታደሰ ደጀኔ (ፕሮፌሰር)፣ የደቡባዊ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ሃፍቱ ኪሮስ፣ የደቡባዊ ትግራይ ዞን ፍትሕ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ፀሃየ አለማየሁ፣ የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕረዚደንት ነጋ ዓፈራ (ዶ/ር)፣ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ ሥራ አስፈፃሚዎች፣ የሕግ ተማሪዎች እንዲሁም የከተማ ማይጨው እና ደቡባዊ ትግራይ ዞን አመራር እና ፍትሕ ባለሙያዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ዛሬ ህዳር 28/ 2017 ዓ.ም በድምቀት ተመርቋል።
የትምህርት ቤቱ ነጻ የሕግ ድጋፍ ማእከል ቁልፍ ዓላማ ዕውቀት ወደ ተግባር በማሽረፍ ዓቅም ሌላቸው የማሕበረሰቡ ክፍል በተለይም አካል ጉዳተኞች፣ ሴቶች፣ ህፃናት እና አረጋውያን ነጻ የሕግ ድጋፍ በማድረግ ፍትሕ የማግኘት መብትን ማረጋገጥ ነው።
ነጻ የሕግ ድጋፍ ማእከሉ በዋናነት አገር በቀል የግጭት መፍቻ ድጋፍ ክፍል፣ የወንጀል እና የፍትሐብሔር ጉዳዮች ማማከሪያ እና የሕግ ተማሪዎች በተግባር የሚማሩበት ክፍሎች ያካተተ ሆኖ ዘመናዊ የቢሮ እቃ የተሟላለት እንደሆነ በጉብኝት ስነ-ስርዓቱ ተመልክተናል።
ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ በምረቃው ስነ ስርዓት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ የራያ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ባደረጋችሁት ብርቱ ጥረት ይህ ነጻ የሕግ ድጋፍ ማእከል በድምቀት ማስመረቃችሁን እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ራያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰቡን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ቁልፍ ተግባራት እየሰራ መምጣቱን ገልፀው በሌሎች የዘገየንባቸው ጉዳዮችም ካሉ በሂደት በተጠናከረ መንገድ የምንሰራ ይሆናል ብለዋል።
ራያ ዩኒቨርሲቲ የ4ኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ ቢሆንም ባለው ጠንካራ የየዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ፣ አመራሮች፣ መምህራን፣ አስተዳደር ሰራተኞች እና ተማሪዎች ተቀናጅተው ውጤታማ ስራዎች በመስራታቸው በፌደራል የፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት፣ የሕግ ትምህርት ቤቶች ኮንሰርቲየም እና የኢትዮጵያ ሕግ ትምህርት ቤቶች ማህበር በጋራ በአዘጋጁት የእውቅና እና የሽልማት ፕሮግራም የራያ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት በ2016 ዓ/ም በሕግ ትምህርት የመውጫ ፈተና የተፈተኑትን ተማሪዎች በማሳለፍ በሀገር ደረጃ 2ኛ በመውጣት የዋንጫ እና የእውቅና ምስክር ወረቀት ተሸላሚ መሆኑን የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ያመላክታል ያሉት ደግሞ አቶ ሃፍቱ ኪሮስ ናቸው።
አቶ ሃፍቱ ኪሮስ አክለው እንደገለፁት፤ ዩኒቨርሲቲው የዞናችን ማህበረሰብ ላለበት የፍትሕ ችግር ለመቅረፍ ነጻ የሕግ ድጋፍ ማእከል ማቋቋሙን የህዝብ ተቋም መሆኑን ያስመሰከረበት እና በቀጣይም ለዩኒቨርሲቲው ውጤታማነት የሥራ አመራር ቦርዱ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
አቶ ፀሃየ አለማየሁ በበኩላቸው በራያ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት የተቋቋመ ነጻ የሕግ ድጋፍ ማእከል ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እና የማህበረሰባችንን የፍትሕ ችግር ለመፍታት ያሉብን የሰው ሃይል እጥረት እና የዓቅም ውሱንነት ለመሙላት የሚደግፍ ነው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በራያ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር እና የዩኒቨርሲቲው ነጻ የህግ ድጋፍ ማእከል አስተባባሪ የሆኑት መምህር ሸዊት ግርማይ ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ነጻ የህግ ድጋፍ ማእከል ፍትሕ እና ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ እና በተለይ ችግር ያለባቸው ህፃናት፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን በማእከሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።
ዶ/ር ነጋ ዓፈራ ‘ዕውቀት ለማህበረሰብ ለውጥ’ የሚለውን ዩኒቨርስቲያችን መመሪያ ተግብረናል ያሉ ሲሆን ሁሉም ኮሌጆች ከሕግ ትምህርት ቤት ልምድ በመውሰድ የላቀ ስራ ለመስራት ዝግጁ እንዲሆኑ በማሳሰብ ለትምህርት ቤቱ ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል።
የራያ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ዲን መምህር መሐመድ ባዩ ባስተላለፉት መልእክት ዕውቀት ለማህበረሰባዊ ለውጥ የሚል የዩኒቨርሲቲያችን መሪ ቃል በመከተል ባለን የሕግ ዕውቀት የማህበረሰባችን የፍትህ ችግር ለመቅረፍ ትልቅ እርምጃ የሄድንበት ስራ ነው በማለት ይህ ነጻ የሕግ ድጋፍ ማእከል ለአገልግሎት ዝግጁ እንዲሆን የዩኒቨርሲቲው አመራሮች እና UASID/OTI/ESP ላደረጉት ውጤታማ ድጋፍ አመስግነዋል።
ተሳታፊዎች በበኩላቸው ራያ ዩኒቨርሲቲ ነጻ የሕግ ድጋፍ ማእከል መክፈቱ መደሰታቸውን ገልፀው በተለይ ማእከሉ የተግባር ትምህርት ለመውሰድ፣ የማህበረሰቡ የፍትሕ ችግር ለመቅረፍ ወሳኝ ነው በማለት ለማእከሉ ውጤታማነት ቀጣይነት ያለው ክትትል እና ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አመላክቷል።
በተያያዘ ዜና በስነ ስርዓቱ ራያ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት ቤት ያገኘውን የዋንጫ እና የሽልማት ምስክር ወረቀት መምህር መሐመድ ባዩ እና አቶ ሃፍቱ ኪሮስ ለዩኒቨርሲቲው ፕረዚደንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ አስረክበዋል።
በመጨረሻም ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ በመዝጊያ ንግግራቸው ራያ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ እያደረገ ያለው የተቀናጀ ስራ አጠናክሮ ይቀጥልበታል በማለት ለማእከሉ የሚያስፈልገውን ግብአት እንዲሟላ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን በማለት ተናግረዋል።

ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ህዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም

ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!

የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
****************************************