የራያ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ከ USAID/OTI ESP ጋር በመተባበር “ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች” በሚል ርእስ ከሚመለከታቸው ቁልፍ አጋር አካላት ኮንፈረንስ አካሄደ።

የራያ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ከUSAID/OTI ESP ጋር በመተባበር “ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች” በሚል ርእስ ከትግራይ ክልል ፍትህ አካላት፣ ደቡባዊ ትግራይ ዞን አመራሮች፣ የፍትህ አካላት፣ ሀገር ሽማግሌዎች፣ ሃይማኖት መሪዎች፣ ሃይማኖት ተቋማት ፍርድ ቤቶች እንዲሁም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ የዘርፉ መሁራን እና የራዩ አመራሮች ጋር በማይጨው ከተማ ዛሬ ነሐሴ 25/2016 ዓ/ም ኮንፈረንስ አካሄዷል።
የኮንፈረንሱ ዓላማ፤ ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በተመለከተ ለቁልፍ አጋር የፍትህ አካላት፣ ሀገር ሽማግሌዎች፣ ሀይማኖት መሪዎች ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ለምርምር፣ ህግ ለማርቀቅ ግብአት ለመፍጠር እንዲሁም እያጋሙ ያሉ ችግሮች በመለየት መፍትሄዎች ለማበጀት ነው።
ዩኒቨርሲቲውን በመወከል የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት መ/ር ህንፃ ገ/ገርግስ፤ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚታዩ አለመግባባቶች እና ግጭቶች ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች በመጠቀም ሰላማዊ እና ገንቢ በሆነ መንገድ እንዲፈቱ እና ተቋማቱ የምርምር ማእከላት እንዲሆኑ ይሰራል ብለዋል።
የደቡባዊ ትግራይ ዞን ማህበራዊ ጉዳይ ሀላፊ አቶ ረዳኢ ልበሎ በበኩላቸው፤ ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች በዞኑ ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ እና በማህበረሰባችን ዘንድ መልካም ግንኙነት ለመፍጠር እና ለተቋማቱ ተገቢውን ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
የUSAID/OTI ESP ሀላፊ አቶ ተስፋማርያም ገብረመድህን፤ በኮንፈረንሱ ለተገኙ ቁልፍ አጋር አካላት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ካስተላለፉ በኃላ በተለያዩ አከባቢዎች ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በማጠናከር በማህበረሰቡ ዘንድ የሚታዩ አለመግባባቶች እና ግጭቶች ለማጥፋት፣ የፍትሕ መጓደልን እና የማህበረሰብ ቀውስ ለመፍታት ድርጅታችን የተለያዩ ስራዎች እየሰራ መጥቷል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት በርሀ ገሰሰ በሰጡት ሙያዊ ማብራርያ፤ የሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች ምንነት፣ ታሪካዊ ዳራ፣ ዓይነቶች፣ ባህርያት፣ ጠቀሜታ፣ ውጤታማነት፣ የኢትዮጵያ ፍትሐ-ብሔራዊ እና ወንጀል ጉዳዮች በሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች፣ የግልግል ዳኝነት በዝርዝር አቅርበዋል።
የሕግ ትምህርት ክፍል ሀላፊ የሆኑት መ/ር በረከት አስመላሽ በበኩላቸው፤ ዓለም አቀፍ የግጭት አፈታት አማራጮች ምንነት፣ ዓይነቶች፣ ባህርያት እና ተሞክሮዎች እንዲሁም ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነትን በተመለከተ ሙያዊ ማብራርያ ሰጥተዋል።
የራዩ ሕግ ትምህርት ቤት ዲን መ/ር መሓመድ ባዩ፤ የሐሳብ እና ተግባር ለውጥ በሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በተመለከተ ባቀረቡት የማጠቃላያ ሙያዊ ማብራርያ፤ ከዚህ በፊት ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች ለማዘመን የተለያዩ ጥናትና ምርምር ቢደረጉም ተጨባጭ ለውጥ አላመጡም ብለዋል። መ/ር መሓመድ ባዩ አክለው ሀገር በቀል የግጭት አፈታት አማራጮች የጥናትና ምርምር ማእከል እና ቱሪዝም መሰህብ ለማድረግ ተግባራዊ መፍትሄ መወሰድ አለበት ብለዋል።
ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ጋር በተደረገ ውይይት፤ ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች መልካም ተሞክሮ፣ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችና መፍትሄዎች ተነስተው በሚመለከታቸው አካላት ማብራርያ ተሰጥቷል።
*****************************************
ራያ ዩኒቨርሲቲ
ነሐሴ 25/2016 ዓ/ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
****************************************