የራያ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትመህርት ቤት ከኢትዮጵያ ሕግ ትምህርት ቤቶች ማሕበር (Ethiopian Law School Association) የሕግ መጻሕፍቶች በስጦታ አገኘ

የራያ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት በርከት ያሉ ለሕግ ትምህርት አጋዥ የሆኑና በገበያ የማይገኙ ለመማር ማስተማር እና ምርምር የሚያገለግሉ እና ለተማሪዎች እጅግ ጠቃሚ የሆኑ የሕግ መጻሕፍቶች ከኢትዮጵያ ሕግ ትምህርት ቤቶች ማሕበር (Ethiopian Law School Association) በማህበሩ ፕረዚደንት አቶ ደርሶልኝ የኔአባት በኩል አግኝቷል።
የራያ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ዲን መምህር መሐመድ ባዩ ከማህበሩ የተገኘውን የሕግ መጻሕፍቶች ለዩኒቨርሲቲው አካ/ምር/ ቴክ/ ሽግ/ ማሕ/ አገ/ ምክትል ፕረዚደንት ዶ/ር ነጋ ዓፈራ ታህሳስ 10/ 2017 ዓ/ም አስረክበዋል።
በርክክብ ስነ ስርዓቱ የሕግ ትምህርት ቤት ዲን መምህር መሓመድ ባዩ ባስተላለፉት መልእክት የኢትዮጵያ ሕግ ትምህርት ቤቶች ማሕበር ላደረገላቸው የመጻህፍት ድጋፍ በማመስገን በቀጣይም ከማህበሩ ግንኙነታችንን በማጠናከር ውጤታማ ስራዎች እንሰራለን ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕረዚደንት ተወካይ ዶ/ር ነጋ ዓፈራ ባደረጉት ንግግር የሕግ ትምህርት ቤት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በማድነቅ ለኢትዮጵያ ሕግ ትምህርት ቤቶች ማህበርም “ቁም ነገረኛ ማህበር” በማለት ለማህበሩ ያላቸውን ታላቅ ምስጋና አቅርበዋል።
ዶ/ር ነጋ ዓፈራ አክለውም በዕለቱ ለተገኙ የሕግ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው አርአያ ሆነው ትምህርታቸው በርትተው እንዲከታተሉ እና ሌሎች ኮሌጆችም ይህን መልካም ስራ ሊከተሉት እንደሚገባ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የሕግ ተማሪዎቹ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ሕግ ትምህርት ቤቶች ማሕበር የተደረገ የሕግ መጻሕፍት ስጦታ በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እና የፈለጉትን የሕግ መጻሕፍት በቀላሉ በማሰስ ለሃገር አቀፍ የመውጫ ፈተና ዝግጅት እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።

ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ታህሳስ 10/ 2017 ዓ.ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
*****************************************