የራያ ዩኒቨርሲቲ የ2016 ዓ/ም የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2017 ዓ/ም የቁልፍ አፈፃፀም አመላካቾች (KPI) ዕቅድ ከመምህራን እና አስተዳደር ሠራተኞች ጋር ውይይት ተካሄደ።

ዩኒቨርሲቲያችን በ2016 ዓ/ም ያስመዘገበው ዘርፈ ብዙ ውጤት እና የደረሰበትን ከፍታ ለማስቀጠል ትኩረቱን ያደረገ የራያ ዩኒቨርሲቲ የ2016 ዓ/ም የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2017 ዓ/ም የቁልፍ አፈፃፀም አመላካቾች (KPI) ዕቅድ ከዩኒቨርሲቲው መምህራን እና አስተዳደር ሠራተኞች ጋር ዛሬ መስከረም 09/2017 ዓ/ም ውይይት ተደረገ፡፡
በውይይቱ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕረዚደንት ታደሰ ደጀኔ (ፕሮፌሰር) ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ራያ ዩኒቨርሲቲ በ2016 ዓ/ም በተለይ በመማር ማስተማር ሂደቱ ለሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አርአያ የሚሆኑ የተለያዩ ውጤታማ ስራዎች በቅንጅት የሰራ ሲሆን ይህ ስኬት እንዲመዘገብ ትልቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የዩኒቨርሲቲው መምህራንን አመስግነዋል።
ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ በንግግራቸው ከእንግዲህ ከደረስንበት ከፍታ መይም ስኬት ወደ ኋላ መመለስ ወይም መቆም አይቻልም በማለት ለዚህም ሁሉም ሰራተኛ የዩኒቨርሲቲው አምባሳደር ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው አካ/ምር/ቴክ/ሽግ/ማህ/አገልግሎት ምክትል ፕረዚደንት ልዩ ረዳት ዶ/ር መሓመድአወል የሱፍ ባቀረቡት ዕቅድ የዩኒቨርሲቲው ተልዕኮ፣ ራዕይ፣ እሴቶች፣ መሪ ቃል፣ ጠንካራ ጎኖች፣ የነበሩ ክፍተቶችና የተወሰዱ መፍትሄዎች፣ የክትትልና ግምገማ ስርዓት ያካተተ የ2016 ዓ/ም ዓመታዊ የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት እና የቁልፍ አፈፃፀም አመላካቾች (KPI) መሰረት ያደረገ የ2017 ዓ/ም ዕቅድ ስትራቴጂካዊ ዕይታዎች፣ መነሻ ሁኔታዎች፣ ቁልፍና ዓበይት ተግባራት፣ ግቦችና ኢላማዎች፣ ለቀጣይ ትኩረት የሚሹ ተግባራት፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቻቸው፣ የዕቅድ አፈፃፀም ምዕራፎች፣ የአፈፃፀም ክትትልና ግምገማ ሥርዓት፣ የዕቅድና ሪፖርት ግንኙነትና ፍሰት፣ የማስፈፀሚያ ስልቶች፣ የክትትል፣ የቁጥጥርና ድጋፍ ሥርዓት እንዲሁም የዕቅዱ መተግበርያ መርሃ ግብር በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
የራያ ዩኒቨርሲቲ ምርምር፣ ሕትመት እና ሥነ ምግባር ዳይሬክተር መምህር ተመስገን ተስፋይ (ረዳት ፕሮፌሰር) በበኩላቸው የምርምር፣ ሕትመት እና ሥነ ምግባር ዳይሬክቶሬት የ2016 ዓ/ም የዕቅድ አፈፃፀም እና የ2017 ዓ/ም የምርምር፣ ሕትመት እና ሥነ ምግባር ዕቅድ መግቢያ፣ የምርምር ማእከላት (Thematic Areas)፣ ግቦችና ኢላማዎች፣ ጠንካራ ጎኖች፣ የነበሩ ክፍተቶችና የተወሰዱ መፍትሄዎች፣ የዳይሬክቶሬቱ ዝርዝር ተግባራት ሀላፊነት፣ ከ2011 ዓ/ም እስከ 2013 የተሰሩ ዓበይት የምርምር ስራዎች፣ የምርምር በጀት ምንጮች ማለትም የመንግስት፣ ከወዩኒቨርሲቲው ውስጥ ገቢ እና ከዩኒቨርሲቲ ውጭ ካሉ አካላት እንዲሁም በ2017 ዓ/ም ትኩረት የሚሹ ቁልፍ እና ዓበይት ተግባራት ገለፃ አድርገዋል፡፡
የራያ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክተር መምህር ደባሲ ግደይ የ2016 ዓ/ም የዩኒቨርሲቲው ቴክኖሊጂ ሽግግር እና ዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስር የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማና ሪፖርት እንዲሁም የነበሩ ጥንካሬዎች፣ያጋጠሙ ችግሮች እና መፍትሔዎች፣ አቅርበዋል፡፡
መምህር ደባሲ ግደይ በገለፃቸው የቁልፍ አፈፃፀም አመላካቾች (KPI) መሰረት ያደረገ የ2017 ዓ/ም ዕቅድ መግቢያ፣ የዕቅዱ መነሻ፣ ዓላማ፣ ቁልፍ እና ዓበይት ተግባራት፣ ግቦችና ኢላማዎ ለቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች፣ የዕቅድ አፈፃፀም ምዕራፎች፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች እና መፍትሔዎች ሲያቀርቡ በተለይም ለቀጣይ ዓመት ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማካሄድ የማህበረሰብን ችግር ለመቅረፍ ይሰራል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ከተሳታፊ መምህራን ለተነሱ የተለያዩ ሀሳብ-አስተያየቶች ኣነ ጥያቄዎች በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ምላሽ እና ማብራርያ ተሰጥቷል፡፡
***************************************
ራያ ዩኒቨርሲቲ
መስከረም 09/2017 ዓ/
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
*****************************************