የዓቅም ማሻሻያ የትምኅርት መርኃ ግብር (Remedial Program) ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ስኬታማ ውጤት ለማምጣት የላቀ ትጋት እንደሚጠበቅባቸው ተጠቆመ።

ይህ የተገለጸው ራያ ዩኒቨርሲቲ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር በ2017 ዓ.ም የተመደቡለትን የዓቅም ማሻሻያ የትምህርት መርኃ ግብር (Remedial Program) ተማሪዎች ጥር 15 እና 16 /2017 ዓ.ም በተሳካ መንገድ ተቀብሎ ዛሬ ጥር 18/ 2017 ዓ.ም ማብራሪያ (Orientation) በሰጠበት ወቅት ነው።
ማብራሪያውን (Orientation) የሰጡት በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ስብዕና ግንባታ ምክትል ዲን መምህር መንግስቱ ጠዓመ ሲሆኑ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተማሩትን ትምህርት የመከለስ ሥራ እንደሚሰራና ተማሪዎቹ በትምህርታቸው ስኬታማ በመሆን እንደ የባለፈው ዓመት የዓቅም ማሻሻያ የትምህርት መርኃ ግብር (Remedial Program) ተማሪዎች 100% ለማለፍ የላቀ ትጋት እንደሚጠበቅባቸው እና ይህ ውጤት እንዲሳካም ዩኒቨርሲቲው በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።
ይህ መርኃ ግብር ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የተሰጠ ሁለተኛ ዕድል በመሆኑ ተማሪዎች በሚኖራቸው የግቢ ቆይታ የተሰጣቸውን መልካም ዕድል ሳያባክኑ በአግባቡ ሊጠቀሙ እንደሚገባ እና ዩኒቨርሲቲ ብዝኃ ማንነት ያለበት ተቋም በመሆኑ ተባብሮና ተቻችሎ የመኖር ባህልን በማዳበር ቤተሰባዊ ግንኙነትን በማዳበር መብትን መጠቀምና ግዴታን መወጣት እንዳለባቸው ምክትል ዲኑ አክለው ገልጸዋል።
በመርኃ ግብሩ ሀገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዲሲፕሊን መመሪያዎች እና የተማሪዎች አገልግሎት ዘርፍ ማለትም የካፌ፣ መኝታ፣ ህክምናና መዝናኛ እንዲሁም በተማሪዎች ኅብረት የሚሰጡ አገልግሎቶች ዘርፍ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን የአካዳሚክ፣ የሬጂስትራር፣ የመርኃ ግብሩ አስተባባሪዎች፣ የአስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች እና የተማሪዎች ኅብረት አባላት ተሳትፈዋል።
በመጨረሻም ተማሪዎቹ ራያ ዩኒቨርሲቲ መመደባቸውን ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸው ትምህርታቸውን በአግባቡ ተከታትለው ውጤታማ ለመሆን እንደሚጥሩ ተናግረዋል።

ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ጥር 18 ቀን 2017 ዓ/ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
****************************************