የዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት በተዘጋጀው የ2017 ዓ/ም በጀት ዕቅድና የአፈፃፀም ውል ገምግመው ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ ካውንስል አባላት ዛሬ ሀሙስ መጋቢት 12/2016 ዓ/ም በሰኔት የመሰብሰብያ አዳራሽ ባደረጉት ስብሰባ በዩኒቨርሲቲው ስትራተጂክ ጉዳዮች ሥራ አሥፈፃሚ አቶ ሃ/ኪሮስ ከበደ ባቀረቡት የ2017 ዓ/ም መደበኛ እና ካፒታል በጀት ዕቅድ የወጪ ሂሳብ መደቦች (Chart of Account) መሰረት በማድረግ የበጀት ሽንሸና ገምግመው ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡
ስብሰባው የመሩት የዩኒቨርሲቲው ፕረዚደንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ የ2017 ዓ/ም የዩኒቨርሲቲው በጀት ቁልፍ ስራዎች ትኩረት ሰጥተን በመስራት ውጤታማ በሆነ መንገድ እንጠቀማለን ብለዋል፡፡
በቀረበው የበጀት ዕቅድ መሰረት የዩኒቨርሲቲው የ2017 ዓ/ም መደበኛ በጀት ብር 405,799,820 ሲሆን ካፒታል በጀት ደግሞ ብር 350,000,000 ጠቅላላ ድምር በጀት ብር 755,799,820 መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ እንደ የዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት ገለፃ የ2017 ዓ/ም በጀት ከነበርንበት ችግር አንፃር ሲታይ በቂ እንዳልሆነ ገምግመዋል፡፡
የበጀት ዕቅዱ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ካውንስል መጋቢት 11/2016 ዓ/ም የገመገመው ሲሆን ቀጣይ ሳምንት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ያፀድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል::
ተሳታፊዎች በቀረበው ዝርዝር በጀት በተመለከተ የተለያዩ ሀሳቦች እና ጥያቄዎች ያነሱ ሲሆን የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እና ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡
በተጨማሪም የካውንስል አባላቱ በፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ የቀረበ የአፈፃፀም ውል መግብያ፣ አስፈላጊነት፣ ዓላማ፣ ጠቀሜታ፣ ተግዳሮቶች፣ ፍኖተ ካርታ እንዲሁም ትግበራ ዙርያ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡
የካውንስል አባላቱ እንደገለፁት የአፈፃፀም ውል የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ቁልፍ ስራቸውን በጥራት፣ ሀላፊነት፣ ተጠያቂነትና ለመስራት ስለሚያግዝ ከሚያዝያ 01/2016 ዓ/ም ወደ ተግባር መግባት አለበት ብለዋል፡፡
**********************
ራያ ዩኒቨርሲቲ
መጋቢት 12/2016 ዓ/ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አሥፈፃሚ