የራያ ዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትሥሥር ዳይሬክቶሬት ያዘጋጀው እና “የዩኒቨርሲቲዎች እና ኢንደስትሪዎች ጠንካራ ትሥሥር ለውጤታማ ፈጠራ!” በሚል መሪ ቃል የውይይት መድረክ ጥር 06/ 2017 ዓ.ም በራያ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ፡፡
የውይይት መርኃ ግብሩ ቁልፍ ዓላማ የዩኒቨርሲቲዎች እና ኢንደስትሪዎች ትሥሥር ለማጠናከር እና ተቀናጅቶ በጋራ መሥራት በሚያስችል ሁኔታ ለመምከር ነው፡፡
በውይይቱ የራያ፣ አክሱም፣ ዓዲግራት እና መቐለ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የትግራይ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ ባለሙያዎች እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉ ሲሆን የዩኒቨርሲቲዎች እና ኢንደስትሪዎች ትሥሥር ለማጠናከር እንዲሁም ያሉ መልካም ተሞክሮዎች ለመለዋወጥ እና የተሰሩ ሥራዎች ቀርበው ፍሬያማ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በዩኒቨርሲቲዎች እና ኢንደስትሪዎች ያለውን ትሥሥር ለማጠናከር አልሞ በተዘጋጀው የውይይት መርኃ ግብር ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የራያ ዩኒቨርሲቲ ፕረዚደንት ታደሰ ደጀኔ (ፕሮፌሰር)፤ በዩኒቨርሲቲዎች እና ኢንደስትሪዎች ያለውን ትሥሥር በማጠናከር እና ተቀናጅንተን ከልብ በመስራት ዩኒቨርሲቲዎች ለኢንደስትሪዎች የገበያ ማእከል እንዲሆኑ በማድረግ ችግር ፈቺ እና የተግባር ተማሪዎች በማፍራት ለህዝባችን እና ሃገራችን ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርብናል ብለዋል፡፡
የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትሥሥር ተሞክሮዎች፣ ችግሮችና መፍትሔዎቻው እና ለቀጣይ የሚሰሩ ስራዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትሥሥር ዲክላሬሽን (Declaration) ይዘት፣ ዓላማ፣ ጠቀሜታ እና ትሥሥሩን ለማጠናከር በጋራ የሚሰሩ የጋራ አጀንዳዎች ዶ/ር ሰዓረ ታጀበ አቅርበዋል፡፡
የራያ ዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትሥሥር ዳይሬክተር መምህር አስመረት ኪዳነ በበኩላቸው ራያ ዩኒቨርሲቲ በትሥሥሩ ዘርፍ የሰራቸው ስራዎች፣ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች እና የተወሰዱ መፍትሔዎች፣ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎች እና ለቀጣይ የሚሰሩ ስራዎች በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች የዩኒቨርሲቲዎች እና ኢንደስትሪዎች ትሥሥር በማጠናከር ዙርያ የተለያዩ ሀሳብ አስተያየቶች አንስተው በሚመለከተቻው አካላት ምላሽ እና ማብራሪያ ተሠጥቷል።
በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲዎች እና ኢንደስትሪዎች ትሥሥር ለማጠናከር እና ቀጣይነት ያለው ትኩረት በመስጠት ኢንደስትሪዎች ከዩኒቨርሲቲዎች ትልቅ ዓቅም እንዲያገኙ የሚያስችል የጋራ መግባቢያ ሰነድ (MoU Draft) በዶ/ር ገ/መስቀል ገ/ማርያም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በተያያዘ ዜና በዩኒቨርሲቲው እየተሰሩ ያሉ የምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ መሰረተ ልማት እና የግቢ ውበት ስራዎች በውይይቱ ተሳታፊዎች ጉብኝት ተደርጎባቸዋል።
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ጥር 07/ 2017 ዓ.ም
ዕውቀት ለማኅበረሠባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አሥፈጻሚ
******************************************