ዩኒቨርሲቲው በመጀመርያና ሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸው 487 ተማሪዎች ለ3ኛ ዙር በደማቅ ስነ ስርዓት አስመረቀ።

ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 487 የመጀመርያና ሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 25/2016 ዓ/ም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ንግድና ቀጠናዎች ትስስር ሚኒስቴር ዲኤታና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የተከበሩ ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ እና የትግራይ ክልል ፕረዚደንት የተከበሩ አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ሌሎች የፌደራል እና የትግራይ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች እና ማህበረሰብ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት አዲስ በተመረቀው አዳራሽ በደማቅ ስነ ስርዓት አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው በመደበኛ የትምህርት መርሃ ግብር 57 ሴት ተማሪዎች የሚገኙበት 269 ወንድ ተማሪዎች በድምሩ 326 ተማሪዎች አስመርቋል። በተከታታይ የትምህርት መርሃ ግብር በቅድመ ምረቃ 11 ወንድ ተማሪዎች እና 9 ሴት ተማሪዎች በድምሩ 20 ተማሪዎች ሲመረቁ በድህረ ምረቃ ደግሞ 25 ሴት ተማሪዎች የሚገኙበት 116 ወንድ ተማሪዎች በድምሩ 141 ተማሪዎች ተመርቀዋል።
በምረቃው ስነ ስርዓት የዩኒቨርሲቲው ፕረዚደንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ ባደረጉት ንግግር ለ2016 ዓ/ም 3ኛ ዙር ተመራቂ ተማሪዎችና የተመራቂ ተማሪዎች ቤተሰብ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ራያ ዩኒቨርሲቲ በአስቸጋሪ የጦርነት ጊዜያት ሆኖ በ2013 ዓ/ም ተማሪዎቹን ሁለት ጊዜ ያስመረቀ ብቸኛ ዩኒቨርሲቲ ነው ብለዋል።
ፕሮፌሰር ታደሰ እንደተናገሩት በመውጫ ፈተና አስፈትነን 97.55% ተማሪዎች በማሳለፍ ከኢትዮጵያ 1ኛ ደረጃ መያዛችን፣ ከኬንሳስ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በተገኘ የ$100,000 ፈንድ በጠብታ መስኖ እየለማ የሚገኝ ከ3 ሄክተር በላይ አትክልትና ፍራፍሬ ችግኝ የተሸፈነ ማሳ ማዘጋጀታችን፣ እንስሳት ማድለብ ስራ እንዲሁም ለአከባቢው ማህበረሰብ ተምሳሌት የሆኑ ስራዎች በቅንጅት መስራታችን ራእያችን ለማሳካት ያግዘናል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የተከበሩ ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር ተመራቂ ተማሪዎች ጠንክራችሁ ተምራችሁ ለዚህ ታሪካዊ የምረቃ በዓል መብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት መመረቅ የመጨረሻ ስኬት ሳይሆን የህይወት ጎዳና ለውጥ የመጀመሪያ እርምጃ በመሆኑ በተሰማራችሁበት የስራ ዘርፍ ውጤታማ መሆን ይጠበቅባችኃል ብለዋል።
ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ አክለው እንደገለፁት ይህ ውጤት እንዲመጣ የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ ከፍተኛ አመራሮች እና ማህበረሰብ ተቀናጅተን መስራታችን ነው በማለት የፌደራል መንግስት በመደበልን በጀት በዩኒቨርሲቲው በ2.2 ቢልዮን ብር የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተሰርተው እንዲመረቁ፣ በ2017 ዓ/ም ዘመናዊ የመምህራን መኖርያ እንዲገነባ፣ በ2017 ዓ/ም 30 ተማሪዎች ባለ ምጡቅ አእምሮ የሆኑ የ9ኛ ክፍል የአከባቢው ተማሪዎች መቀበል የሚያስችል የተሟላ የቤተ ሙከራ፣ ቤተ መፃህፍት፣ ማደርያ ክፍልና መማርያ ክፍል የያዘ የማይጨው ሰማእታት አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ እንዲጀመር ተሰርቷል ብለዋል።
በምረቃው ስነ ስርዓት በዩኒቨርሲቲው የተሰራ “ራያ ዩኒቨርሲቲ ከየት – ወዴት” በሚል ርእስ የተዘጋጀ ዘጋቢ ፊልም እና “ላንዳ የዩኒቨርሲቲው መፅሄት” ተመርቀዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች እና የተመራቂ ተማሪዎች ቤተሰብ እንኳን ደስ አላችሁ!
******************