በዩኒቨርሲቲው ለ2016 ዓ/ም እጩ ተመራቂ ተማሪዎች በመውጫ ፈተና ሞዳል በዩኒቨርስቲው መምህራን የተዘጋጀ የመሞከሪያ ፈተና (Model Exam) ተሰጠ።

የራያ ዩኒቨርሲቲ የ2016 ዓ/ም እጩ ተመራቂ ተማሪዎች በመውጫ ፈተና ሞዳል Safe Exam Browser በዩኒቨርስቲው መምህራን የተዘጋጀ የመሞከሪያ ፈተና (Model Exam) ዛሬ ጥር 25/2016 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው የፈተና ማእከል ተሰጠ።
ፈተናው በዩኒቨርሲቲው የፈተና ማእከል አስተባባሪ አማካኝነት ከመረጃ እና መገናኛ ቴክኖሎጂ (ICT)፣ ከምፒውተር ሳይንስ (Computer Science) እና መረጃ ቴክኖሎጂ (IT) ትምህርት ክፍሎች በተውጣጡ ባለሙያዎች ሲስተሙ ወደሚቀበለው ፎርማት ተቀይሮ ወደ ትምህርት ሚኒስቴር በመላክ እና ወደ ሲስተሙ እንዲጫን (Upload) ተደርጓል።
በትምህርት ሚኒስቴር የሚገኙ ባለሙያዎች ባደረጉት ቀና ትብብር የተጠቃሚዎች ስም (User Name) እና ሚስጢራዊ ቁልፍ (Password) ለተማሪዎች እና ለመምህራን በመፍጠርና በመላክ ፈተናው በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ተደርጓል።
በመሞከርያ ፈተናው (Model Exam) በ14 የትምህርት መስኮች 84 እጩ ተመራቂ ተማሪዎችን ማስፈተን ተችሏል።
የፈተናው ዋና ዓላማ ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ ስለሚያስፈትን እጩ ተመራቂ ተማሪዎች ከሲስተሙ ጋር በማላመድ ለዋናው መውጫ ፈተና (Exit Exam) ዝግጁ ለማድረግ እና በራስ መተማመናቸውን በማሳደግ ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ለማስቻል ያለመ ነው።
የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕረዚደንት ዶ/ር ነጋ ዓፈራ፣ ኮሌጅ ዲኖች፣ የትምህርት ክፍል ሀላፊዎች እና የተያዩ አመራሮች በአካል በመገኘት ፈተናውን ተመልክተውታል።
የፈተና ማእከሉ አስተባባሪ መምህር ተስፋይ ሀረገወይን እንደገለፁት ከፈተናው ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ቴክኒካል ችግሮች በዩኒቨርሲቲያችን ባለሙያዎች እና ከትምህርት ሚኒስቴር ባለሙያዎች ጋር በስልክ እየተነጋገርን በመፍታት ፈተናው በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ችለናል ብለዋል።
መምህር ተስፋይ አክለው ፈተናው ውጤታማና የተሳካ እንዲሆን የሚመለከታቸው የዩኒቨርስቲው አመራሮች፣ መምህራን እና ባለሙያዎች የጎላ ተሳትፎ አበርክተዋል ብለዋል።
***********************
ራያ ዩኒቨርሲቲ
ጥር 25/2016 ዓ/ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
👇👇👇