ለዩኒቨርሲቲው የከፍተኛ እና መካከለኛ የአሥተዳደር አመራሮች ተግባራዊ የውጤት ተኮር ስትራቴጂ (BSC) የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጠ።

በዩኒቨርሲቲው የስትራቴጂ ጉዳዮች ሥራ አስፈፃሚ የተዘጋጀ ለከፍተኛ እና መካከለኛ የአሥተዳደር አመራሮች የውጤት ተኮር ስትራቴጂ (BSC) እና ተዛማጅ ጉዳዮች በማይጨው ከተማ ታደለ ሆቴል ከግንቦት 26-27/2016 ዓ/ም ለሁለት ቀናት የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጥቷል።
በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕረዚደንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ በዩኒቨርሲቲያችን እየታየ ያለው ውጤት ተኮር ስትራቴጂ፣ የዕቅድና ሪፖርት ክፍተት ለመሙላት ይህ ስልጠና ወሳኝ ነው ብለዋል።
የራያ ዩኒቨርሲቲ ስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈፃሚ በዩኒቨርሲቲው ያሉ ሁሉም ፅ/ቤቶች በዕቅድ፣ ሪፖርት እና የሰራተኞች የሥራ አፈፃፀም በተመለከተ ምልከታ ያደረጉ ሲሆን በምልከታው የታዩ ጠንካራ ክንውኖች እና ሊስተካከሉ የሚገባቸው ጉዳዮች በመ/ር ጋሻው ቀርቧል።
ስልጠናውን የሰጡት የስትራቴጂክ ጉዳዮች ቡድን መሪ የሆኑት መ/ር ጋሻው ተፈሪ ሲሆኑ የውጤት ተኮር ስትራቴጂ (BSC) ጽንሰ ሀሳብ ምንነት፣ ዓላማ፣ ታሪካዊ ዳራ (Background)፣ መርሆች፣ ስኬታማነት፣ ውሱንነት፣ እንዲሁም የክትትልና ግምገማ አስፈላጊነት እና የዕቅድ እና ሪፖርት አቀራረብ ይዘት ገለፃ አድርገዋል።
መ/ር ጋሻው ተፈሪ በስልጠናቸው የቅድመ ሁኔታና ተቋማዊ ዳሰሳ፣ ተቋማዊ ስትራቴጂ፣ ስትራቴጂያዊ ግቦችን ቀረፃ፣ የስትራቴጂክ ካርታ (Map)፣ የአፈፃፀም መለኪያዎች እና አፈጻጸም፣ እርምጃዎች ቀረፃ፣ የአፈፃፀም መረጃ ሥርዓት ዝርጋታ፣ ውጤት ተኮር ዕቅድ በየደረጃው ለፈፃሚ አካላት ማውረድ እና የአፈፃፀም ክትትልና ግምገማ ዝግጅት የሚሉ ዘጠኝ የውጤት ተኮር ስትራቴጂ ግንባታ እና ትግበራ ደረጃዎች ሰፊ ማብራርያ ሰጥተዋል።
ሰልጣኞች በበኩላቸው በየስራ ዘርፉ በመሆን በ4 ቡድኖች ተከፍለው የውጤት ተኮር ስትራቴጂ ግንባታ እና ትግበራ ደረጃዎች የዕቅድ እና ሪፖርት ፎርማት መሰረት ያደረገ ተግባር ተኮር ቡድን ሥራ ሰርተው በተወካዮቻቸው አቅርበዋል።
በመጨረሻም ከሰልጣኞች ለተነሱ ሀሳብ፣ አስተያየት እና ጥያቄዎች በሚመለከታቸው ባለሙያዎች ምላሽ እና ማብራርያ ተሰጥቷል።
*****************************
ራያ ዩኒቨርሲቲ
ግንቦት 28/2016 ዓ/ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
ለበለጠ መረጃ👇👇👇ይመልከቱ።