በራያ ዩኒቨርሲቲ ከ1 ቢልየን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተመረቁ።

በዩኒቨርሲቲው በ2012 ዓ/ም የተጀመሩ እና በጦርነት ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀከቶች ከ1 ቢልየን ብር በላይ ወጪ ተገንብተው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ንግድና ቀጠናዎች ትስስር ሚኒስቴር ዲኤታ እና የራያ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የተከበሩ ዶ/ር ካሳሁን ጎፌን ጨምሮ ሌሎች የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ አስተዳደር ሰራተኞችና የአከባቢው ማህበረሰብ በተገኙበት ዛሬ ሰኔ 24/2016 ዓ/ም በደምቀት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል።
ዛሬ የተመረቁት የዩኒቨርሲቲው የልማት ፕሮጀክቶች ከማይጨው 01 ቀበሌ አዲስ አለም ትምህርት ቤት አስፋልት መታጠፍያ እስከ ዩኒቨርሲቲው በር የተሰራ 740 ሜትር ዘመናዊ የአስፋልት መንገድ እና የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የውሃና መብራት ዝርጋታ፣ የአጥር ግንባታ፣ 2 የተማሪዎች መማርያ ህንፃዎች፣ 4 የተማሪዎች የመኝታ ህንፃዎች፣ 2 የተማሪዎች ልብስ ማጠብያ ህንፃዎች፣ 1 ዘመናዊ አዳራሽ፣ የግቢ ውበት እና መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ የማስተካከል ስራ፣ በጠብታ መስኖ እየለማ የሚገኝ ከ3 ሄክተር በላይ አትክልትና ፍራፍሬ ችግኝ የተሸፈነ ማሳ፣ ከ500 በላይ በጎችና በሬዎች፣ ለአከባቢው ማህበረሰብ ተምሳሌት የሆኑ ስራዎች ናቸው።
የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶቹ የመረቁት የተከበሩ ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ ፕሮጀክቶቹ በፍጥነት፣ ጥራት፣ ጥንቃቄና ታታሪነት እንዲጠናቀቁ ትልቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ አመራሮች፣ ኮንትራክተሮች፣ የስራ ተቋራጭ ተቆጣጣሪዎች እና አማካሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና ተማሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ በማለት በ2017 ዓ/ም ለማጠናቀቅ በእቅድ የተያዙ ፕሮጀክቶችን በጥብቅ ክትትልና ድጋፍ እንዲመሩ በማድረግ አስቀድመው ተጠናቀው እንዲመረቁ ተችሏል ብለዋል።
ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ አክለው እንደገለፁት ራያ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ጥራት፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ዲጂታላይዜሽን፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ የስራ እድል ፈጠራ እና ግቢ ውበት የሰራቸው ውጤታማ ስራዎች ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች አርአያሚ በመሆኑ ለቀጣይ ከዚህ በበለጠ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕረዚደንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ በበኩላቸው በተለያዩ ምክንያቶች በዩኒቨርሲቲው የተቋረጡ ፕሮጀክቶች ኮንትራክተሮች ባደረጉት ጠንካራ ርብርብ ወደ ምረቃ በቅተዋል በማለት ይህ የተሳካ ስራ እንዲሰራ የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ አመራሮች፣ በዩኒቨርሲቲው የተቋቋመ ጥራት ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ሁልጊዜ ዓርብ ፕሮጀክቶቹ በመጎብኘት ገንቢ አስተያየት ለሰጡና የሚመለከታቸው አካላት ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አመስግነዋል።
በምረቃው ስነ ስርዓት ውጤታማ ስራ ለሰሩ ኮንትራክተሮች፣ የግንባታ ባለሙያዎችና የግቢ ውበት ሰራተኞች ከክቡር ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ እጅ ሽልማትና የምስጋና ምስክር ወረቀት ተቀብለዋል።
በመጨረሻም ሀላፊዎቹ በዩኒቨርሲቲው የተሰሩ ስራዎች እና የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ጎብኝተዋል።
*********************************************
ራያ ዩኒቨርሲቲ
ሰኔ 24/2016 ዓ/ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
******************************************