የራያ ዩኒቨርሲቲ ህግ ትምህርት ቤት እና ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ትስስር ለማጠናከር የምክክር መድረክ ተካሄደ።

ራያ ዩኒቨርሲቲ ህግ ትምህርት ቤት ከ USAID/OTI ESP ጋር በመተባበር የራያ ዩኒቨርሲቲ ህግ ትምህርት ቤት እና ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ትስስር ለማጠናከር ከተለያዩ ወረዳዎች የመጡ የማህበራዊ ፍርድ ቤት ሰራተኞች ጋር ሐሙስ መስከረም 16/2017 ዓ/ም በማይጨው ከተማ የምክክር መድረክ ተካሄደ።
የራያ ዩኒቨርሲቲ ህግ ትምህርት ቤት ዲን መምህር መሐመድ ባዩ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የራያ ዩኒቨርሲቲ ህግ ትምህርት ቤት እና ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ያላቸውን ትስስር በማጠናከር በማህበረሰባችን ዘንድ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች እንዲፈቱና የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ ችግሮች ከምንጩ ለማድረቅ የተቋማቱ ሚና ለማጠናከር እንሰራለን ብለዋል።
በራያ ዩኒቨርሲቲ ህግ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት መምህር በርሀ ገሰሰ የማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ስልጣንና ተግባር ለመወሰን ተሻሽሎ የወጣ አዋጅን መሰረት አድርገው ለተሳታፊዎች በሰጡት ሙያዊ ማብራሪያ መሰረት የማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ሚና በዕርቅ፣ የማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ስረ ነገረ ስልጣን ዳይነት በፍትሐ-ብሔር ጉዳዮች፣ የማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ስልጣን የሆኑ እና ያልሆኑ ተግባራት፣ የማህበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች ግዴታዎች እና ከስራ የሚሰናበቱበት ሁኔታዎች፣ በችሎት የሚሰየሙ የዳኞች ብዛትና የፆታ ተዋፅኦ፣ ቅጣት፣ ዋስ፣ እግድ፣ መጥሪያ እና ትዕዛዝ፣ ክስ የመስማት ሂደት፣ የከሳሽ እና ተከሳሽ ጉዳይ፣ ዕርቅ፣ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት፣ የወጪና ኪሳራ ጉዳይ፣ የይግባኝ መብት፣ ውክልና፣ የችሎት ቦታ፣ ጊዜናግልፅነት፣ የውሳኔ አፈፃፀም፣ እንዲሁም ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች የሚከተሉት ስነ ስርዓት፣ ተጠሪነት እና ግንኙነት በዝርዝር ገለፃ አድርገዋል።
ከተለያዩ ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች የመጡ የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የቡድን ውይይት አድርገው በሰጡት ማብራሪያ መሰረት በየስራ ዘርፋቸው ያሉ መልካም ተሞክሮዎች፣ እያጋጠሟቸው ያሉ ችግሮችና የወሰዷቸው መፍትሄዎች በቡድን በተወካዮቻቸው በኩል አቅርበዋል።
በመጨረሻም የ USAID/OTI ESP ተወካይ አቶ ሲሳይ ብሩክ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ከራያ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት ጋር ተቀናጅተን በመስራት የማህበረሰባችን ዘርፈ ብዙ የሰላምና ፀጥታ ችግሮች ለመፍታት ማህበራዊ ፍርድ ቤቶችን በዓቅም ግንባታ፣ ቁሳቁስ፣ ለማጠናከር አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው ስራ እንሰራለን ብለዋል።
****************************************
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ሐሙስ መስከረም 16/2017 ዓ/ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
************************************