የራያ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል አባላት የዩኒቨርሲቲው በአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህበረሰብ ጉድኝት የስራ ዘርፎች የቀረበውን የ2017 ዓ/ም አንደኛ ሩብ ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ዛሬ ጥቅምት 22/2017 ዓ/ም ገምግመዋል።
የራያ ዩኒቨርሲቲ ፕረዚደንት ታደሰ ደጀኔ (ፕሮፌሰር) ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ዩኒቨርሲቲው እየሰራቸው ያሉ ዘርፈ ብዙ ውጤታማ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሁሉም ሰራተኛ ስራውን በእቅድ መሰረት እና በአግባቡ በመስራት ለሚመለከተው አካል ሪፖርቱን በወቅቱ ማቅረብ ይኖርበታል ብለዋል።
የራያ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕረዚደንት ተወካይ ቀሲስ ንጉስ መሰለ (ዶ/ር) የ2017 ዓ/ም አንደኛ ሩብ ዓመት ከተሰሩ ጠንካራ ስራዎች መካከል ነባር መደበኛ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች ተቀብሎ ማስተማር፣ ከመምህራን ጋር የ2016 ዓ/ም ዓመታዊ እቅድ አፈፃፀም እና የ2017 ዓ/ም ዓመታዊ የስራ እቅድ ሰፊ እና ጥልቅ ውይይት ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱ፣ የዩኒቨርሲቲው መገለጫ የሆነውን “ከትምህርት ገበታ መቅረት እንደ ነውር የማድረግ ልምድ” በሚመለከታቸው አካላት ክትትል እና ድጋፍ የተደረገበት የተሳካ ትምህርት የማስጀመር መርሃ ግብር (Day One Class One) መካሄዱ፣ የ 2016 ዓ/ም “Other Social Scince” እና “Other Natural Science” ተማሪዎች ተገቢውን ማብራሪያ (Orientation) በሚመለከታቸው አካላት በመስጠቱ ተማሪዎች የሚፈልጉትን የትምህርት ክፍል እንዲመርጡ መደረጉ፣ በማይጨው ሰማእታት አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 30 በጋርዮሽ ሳይንስ መርሃ ግብር (Science Shared Program) ደግሞ 20 የ9ኛ ክፍል ተማሪዎች ተቀብሎ ጥራት ያለው ትምህርት መሰጠቱ፣ በዩኒቨርሲቲው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ከተፈተኑት 14 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች 13ቱም ማለፋቸው፣ 59 መምህራኖቻችን በ ከፍተኛ ዲፕሎማ መርሃ ግብር (HDP) መመረቃቸው፣ በዩኒቨርሲቲው የነበሩት የዓቅም ማጠናከሪያ መርሃ ግብር (Remedial Program) የወሰዱ ተማሪዎች 100% ማለፋቸው፣ 9 የምርምር፣ የማህበረሰብ ጉድኝት፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስር ፕሮጀክቶች ፀድቀው ወደ ተግባር መግባታቸው፣ ለተመራማሪዎቻችን የምርምር ስነ ምግባር፣ ግዢ ሂደት እና የፋይናንስ ስርዓት አስተዳደር ስልጠና ተሰጥቷል፣ 2000 የአከባቢው አርሶ አደሮች ተጠቃሚ የሚያደርግ እና 800 ኩንታል ይገኝበታል ተብሎ የሚታሰበው በ22 ሄክታር ማሳ የስንዴ ምርጥ ዘር ብዜት ተከናውኖ ወደ ምርት መሰብሰብ ደረጃ መድረሱ፣ ከ Kansas State University በተገኘ የ$ 100,000 ፈንድ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የአትክልት እና ፍራፍሬ ውጤቶች በጠብታ መስኖ የማምረት ስራ መከናወናቸው፣ የስማርት ክፍል እና የአፈር ምርምር ቤተ ሙከራ ማእከል ግንባታ፣ የወተት ላሞች እና የዶሮ እርባታ ቅድመ ዝግጅት ስራዎች፣ ከ CultivAid ጋር በመተባበር የተሰራ የጠብታ መስኖ የአትክልት ምርት፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር የመግባቢያ ሰነዶች መፈረማቸው እንዲሁም የPedagogy እና Leadership ለ50 መምህራን መሰጠቱ አንስተዋል።
ዶ/ር ንጉስ መሰለ አክለው እንደገለፁት የቤተ ሙከራ ህንፃ ውሃ፣ መብራት የሰርቪስ ችግር፣ የመረጃ እና መገናኛ ቴክኖሎጂ ዝርጋታ ክፍተት፣ የSIMS ቴክኒካዊ ችግር፣ የ PhD ትምህርት እድል እጥረት እና የቆላ የምርምር ማእከል አለመኖር እንደ ክፍተት በስራዎቻቸው እንቅፋት እንደፈጠረላቸው እና ደረጃውን የጠበቀ ቤተ ሙከራ ለማደራጀት፣ ንብረቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ለማስገባት እና የሰርቶ ማሳያ ማእከላት ደረጃቸውን የጠበቁ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶባቸው ይሰራል ብለዋል።
የራያ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር እና ልማት ምክትል ፕረዚደንት ዶ/ር ክብሮም ካሕሱ የ2017 ዓ/ም አንደኛ ሩብ ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት የ2017 ዓ/ም እቅድ ክለሳ በማድረግ ስራዎቻቸው የጀመሩ ሲሆን በብቃትና ሰው ሃብት አስተዳደር ዘርፍ የመምህራን እና ሰራተኞች ቅጥር፣ ዝውውር እና የደረጃ እድገት እንዲሁም እየተሰጠ ያለው ቀልጣፋ አገልግሎት፣ ለሶስተኛ ወገን (Outsource) የተሰጠ ስልጠና፣ አቅርቦት እና ፍላጎት ማእከል ያደረገ የተማሪዎች ምግብና አገልግሎት፣ የተማሪዎች አደረጃጀት ተሳትፎ፣ የአገልግሎት ስርዓቱ የተሻሻለ እና ጥራቱን የጠበቀ የመኝታ እና መማርያ ክፍል ማዘጋጀት፣ የኢንተርኔት አገልግሎት ማዘመን፣ የተማሪ ክሊኒክ አገልግሎት ለማሻሻል የመድሃኒት አቅርቦት ማሟላት እና ከለምለም ካርል ውል መታሰሩን፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ግንባታ፣ የተማሪዎች የስነ ልቦና ምክር አገልግሎት እና ስልጠና መሰጠቱ፣ ስማርት ክላስ ግንባታ፣ የግቢ ውበት ስራዎች፣ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር፣ የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ (Landscape) ማስተካከል፣ የተሽከርካሪ አገልግሎት፣ የነዳጅ አቅርቦት ማሟላት፣ ዲጂታል ንብረት አስተዳደር ስርዓት ትግበራ፣ የምህንድስና እና ጥገና ስራዎች፣ የውሃ፣ መብራት፣ ኤሌክትሪክ፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እና የግንባታ ፕሮጀክቶች በዝርዝር ገለፃ አድርገዋል።
ዶ/ር ክብሮም ካሕሱ ጨምረው እንደገለፁት በሩብ ዓመቱ የስልጠና ከፍተት፣ የካይዘን ስርዓት ትግበራ ክፍተት፣ የልምድ ልውውጥ እጥረት፣ ቼክ ሊስት መሰረት ያደረገ ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ክፍተት፣ ተጨማሪ የፋይናንስ ፋይሎች ማከማቻ አለመኖር፣ የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓት ትግበራ ክፍተት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ችግር፣ የደንበኞች ፍላጎት ዳሰሳ እንዲሁም የ EGP ትግበራ መጓተት ካነሷቸው ተግዳሮቶች አንስተው እነዚህ ችግሮች ለመቅረፍ የተወሰዱ መፍትሔዎች እና ለቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችም በዝርዝር አንስተዋል።
በተጨማሪም በቀረበው የስራ አፈፃፀም እና የዩኒቨርሲቲው የ2016 ዓ/ም 4ኛ ሩብ ዓመት የኦዲት ሪፖርት ዙርያ ከካውንስል አባላቱ ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን በውይይቱ ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች በዩኒቨርሲቲው አመራሮች እና በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በመጨረሻም በ2017 ዓ/ም አንደኛ ሩብ ዓመት የተከናወኑ መልካም ስራዎች በማጠናከር ለታዩ ክፍተቶች ደግሞ መፍትሔ በማበጀት በሁለተኛ ሩብ ዓመት ውጤታማ ስራ ሰርተን የዩኒቨርሱቲያችን ከፍታ ማስቀጠል ይጠበቅብናል ሲሉ ፕሮፎሰር ታደሰ ደጀኔ በመዝጊያ ንግግራቸው ገልፀዋል።
*****************************************
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ/ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
*****************************************