ዩኒቨርሲቲው ለ1ኛ ዓመት አዲስ ገቢ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መርሃ ግብር አዘጋጀ

ራያ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎቹን ህዳር 09 እና 10 /2017 ዓ.ም ተቀብሎ ዛሬ ህዳር 12 /2017 ዓ.ም የእንኳን ደህና መጣችሁ መርሃ ግብር አዘጋጀ።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የራያ ዩኒቨርሲቲ ፕረዚደንት ታደሰ ደጀኔ (ፕሮፌሰር) ለተማሪዎቹ ወደ ታሪካዊቷ እና የፍቅር ከተማ ማይጨው እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ራያ ዩኒቨርሲቲ በ2016 ዓ.ም መውጫ ፈተና (Exit Exam) ሁለት ጊዜ አስፈትኖ ከኢትዮጵያ 1ኛ ደረጃ መያዙ፣ በ2016 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው በአቅም ማሻሻያ መርሃ ግብር (Remedial Program) ካስተማራቸው 210 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የ2ኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ተፈትነው 100% ማለፋቸው እና ከትምህርት መቅረት እንደ ነውር የሚታይበት ዩኒቨርሲቲ በመሆኑ በትምህርት ጥራት ትኩረት ሰጥተን መስራታችን ያመላክታል ብለዋል።
ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ አክለው እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው የሚታወቅበት “ሰው ሰው በመሆኑ እንወደዋለን!” የሚል መርህ ተግባራዊ በማድረግ ተማሪዎች ላላቸው የቤተሰብ እና የሃገር አደራ ለማሳካት ውጤታማ የትምህርት ቆይታ እንዲኖራቸው እንሰራለን በማለት ተማሪዎች በትምህርት ቆይታችሁ ለሚገጥማችሁ ፈተና በጥበብ፣ ብልሃት እና መቻቻል ማለፍ ይኖርባችኋል ብለዋል።
የራያ ዩኒቨርሲቲ ዋና ረጂስትራር ዳይሬክተር መ/ር አብርሃ ተካ ለተማሪዎች የ2017 ዓ.ም የትምህርት ቀለንተን (Academic Calendar)፣ የተማሪዎች ምዝገባ ሂደት፣ የስነ ምግባር ሕግ እና ደምብ እንዲሁም የተማሪዎች ምዘና ሂደት ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የተማሪዎች አገልግለሎት ዲን መ/ር ረዳኢ ስብሃቱ በበኩላቸው በተማሪዎች ምግብና፣ መኝታ፣ ክሊኒክ፣ ስፖርት እና መዝናኛ አገልግሎቶች ዙርያ መብትና ግዴታ ለተማሪዎች ገለፃ አድርገዋል።
በመርሃ ግብሩ የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች የባህል ቡድን አነቃቂ እና ባህላዊ ዘፈኖች እና ውዝዋዜዎች እንዲሁም ግጥም ለተማሪዎች አቅርበዋል።
***********************************************
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ሕዳር 12 ቀን 2017 ዓ/ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
***********************************************