ለዩኒቨርሲቲው ሬጂስትራር፣ ቤተ መፃህፍት እና ቤተ መዛግብት ሠራተኞች “የአስተዳደር መሥሪያ ቤት አገልጋይ እና ተገልጋይ ሕጋዊ አንድምታ” ሥልጠና ተሰጠ

በተለያየ ደረጃ ለሚገኙ የራያ ዩኒቨርሲቲ ሬጂስትራር፣ ቤተ መፃህፍት እና ቤተ መዛግብት ሠራተኞች “የአስተዳደር መሥሪያ ቤት አገልጋይ እና ተገልጋይ ሕጋዊ አንድምታ” ሥልጠና ዛሬ ህዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም በመኾኒ ከተማ ሜዳ ራያ ሆቴል ተሰጥቷል።
የሥልጠናውን ቁልፍ ዓላማ በሙያዊ ሥነ ምግባር የሚተማመን ሠራተኛ እንዲኖር ለማድረግ እና የተገልጋይ ተማሪዎች መብት እና ግዴታ ለማረጋገጥ እንዲሁም ግልፅነት እና ተጠያቂነት ለማስፈን ነው።
በሥልጠናው ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕረዚደንት ዶ/ር ነጋ ዓፈራ፤ ሥልጠናው ጥራት ያለው አገልግሎት ለመሥጠት፣ የሠራተኞቻችን ዓቅም ለማሳደግ፣ የታማኝነት ተጠያቂነት ሥርዓት ለመዘርጋት እና ፍትሓዊ አሠራር ለማስፈን አስፈላጊ በመሆኑ ሠልጣኞች የሚሰጠውን ሥልጠና በንቃት በመሳተፍ የሚጠበቅባችሁን ዕውቀትና ልምድ በመቅሰም ወደ ተግባር መቀየር አለባችሁ በማለት ሃሳባቸውን ገልፀዋል፡፡
ሥልጠናውን የሰጡት በራያ ዩኒቨርሲቲ የሕግ አገልግሎት ሥራ አስፈፃሚ መ/ ዳንኤል ሓየሎም (ሊ/አ) ሲሆን በዋናነት የአስተዳደር መሥሪያ ቤት አሠራር አጠቃላይ መርኅ እና የአሥተዳደር መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የሥነ ምግባር ድርጊት ትኩረት ያደረገ ነበር።
መ/ ዳንኤል ሓየሎም (ሊ/አ) በሥልጠናው በተለይ የአስተዳደር መሥሪያ ቤት ኃላፊነት፣ አራቱም የሠራተኞች መመዘኛዎች (ሥነ ምግባር፣ ዕውቀት፣ ክኅሎት እና ችሎታ)፣ የአሰራር ዝርዝር መርኆዎች፣ የሥነ ምግባር እና ኢ-ሥነ ምግባር ተቃርኖ፣ የተገልጋዮች መሠረታዊ መብቶች፣ የተማሪዎች የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት፣ ቃለ-መሐላ፣ የሚያስቀጡ ድርጊቶች፣ የማይገባ ጥቅም፣ በዕዳ የመጠየቅ ኃላፊነት እና አስተዳደራዊ ቅጣቶች (ቀላል እና ከባድ ቅጣቶች) ዝርዝር ሙያዊ ማብራሪያቸውን ሰጥተዋል።
ከሠልጣኞች በተደረገ ውይይት በበኩላቸው በትምህርት ዕድል፣ የሥራ እድገት፣ ዓመታዊ የሥራ ዕረፍት፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያ፣ የሥራ መደብ ዝርዝር ተግባራት (Job Description) እና የመኪና ሰርቪስ ዙርያ ለተነሱ የተለያዩ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች በዶ/ር ነጋ ዓፈራ፣ መ/ር አብርሃ ተካ፣ መ/ር ተክለ ሃ/ኪሮስ እና መ/ዳንኤል ሓየሎም (ሊ/አ) ማብራሪያ እና ምላሽ ተሰጥቷል።
በመጨረሻም ዶ/ር ነጋ ዓፈራ በመዝጊያ ንግግራቸው፤ እንደዚህ ዓይነት ሥልጠናዎች የሠራተኞቻችን ዓቅምና ልዩ ችሎታ ለማሳደግ እንዲሁም መልካም የስራ አካባቢ ለመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ ስላላቸው ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
ሰልጣኞች ከሥልጠናው በኋላ እንደተናገሩት ሥልጠናው ሥራቸውን በታማኝነት፣ ቅንነት እና ተጠያቂነት ለማገልገል ፋይዳው የጎላ ነው በማለት አስተያየታቸውን ገልፀዋል።
************//**********************
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ህዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
*********//**************************