በተለያየ ደረጃ ለሚገኙ የራያ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ክሊኒክ እና የመኝታ አገልግሎት ሠራተኞች የአሥተዳደር መሥሪያ ቤት የአገልጋይ እና የተገልጋይ ሕጋዊ አንድምታ፣ የሥራ መደብ መግለጫ እና የህይወት ክህሎት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ከታህሳስ 12-13/ 2017 ዓ.ም በመኾኒ ከተማ ሜዳ ራያ ሆቴል ተሰጥቷል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናው ተቋማዊ የአሠራር ግልጽነት እና ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ሙያዊ ሥነ ምግባር በተገቢው መንገድ የሚተገብር ሠራተኛ እንዲኖር በማድረግ እና የተገልጋይ ተማሪዎች መብት እና ግዴታ ለማስከበር ያለመ ነው።
የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናው የአሥተዳደር መሥሪያ ቤት አሠራር አጠቃላይ መርኅ እና የአሥተዳደር መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የሥነ ምግባር ድርጊት የሥራ መደብ ዝርዝር መግለጫ እና የህይወት ክህለቶች ትኩረት ያደረገ ነበር።
በራያ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አሥፈጻሚ ዶ/ር ገሰሰ ንጉስ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናው የሠራተኞቻችን ዓቅም ለማሳደግ እና የሚሰጠውን ተቋማዊ አገልግሎት ለማሻሻል አስፈላጊ በመሆኑ ሥልጠናውን መተግበር ይኖርባቹኃል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው የሕግ አገልግሎት ሥራ አሥፈጻሚ መ/ ዳንኤል ሓየሎም (ሊ/አ)፤ የአስተዳደር መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ኃላፊነት፣ ሥነ ምግባር፣ ዕውቀት፣ ክኅሎት እና ችሎታ መሰረት ያደረጉ የሠራተኞች መመዘኛ መስፈርቶች፣ የአሠራር ዝርዝር መርኆዎች፣ የሥነ ምግባር እና ኢ-ሥነ ምግባር ተቃርኖዎች፣ የተገልጋዮች መሠረታዊ መብቶች እና ግዴታዎች፣ የተማሪዎች የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት፣ ቃለ-መሐላ፣ የሚያስቀጡ ድርጊቶች፣ የማይገባ ጥቅም፣ በዕዳ የመጠየቅ ኃላፊነት እና አስተዳደራዊ ቀላል እና ከባድ ቅጣቶች ዝርዝር ሙያዊ ማብራሪያቸውን ሰጥተዋል።
የህይወት ክህሎት ሥልጠና ትኩረት በማድረግ የግል ስብእና፣ ለለውጥ መነሳት፣ ርህራሄ ወይ ልባዊ ድምጠት (Empathy) እና አገልግሎት የሚሹ ደንበኞች (Clients) ሪፈራል ቅፅ የሚሉ አጀንዳዎች ዝርዝር ገለጻ ያደረጉት ደግሞ የራያ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ቡድን መሪ አቶ ገ/ሄር ወልዱ ናቸው።
የተማሪዎች አገልግሎት ዲን መምህር ረዳኢ ስብሃቱ በበኩላቸው የሥራ ተኮር ክንውን ሥልጠና የሰጡ ሲሆን የተማሪዎች መኝታ አገልግሎት ሥራ መደብ ዝርዝር መግለጫ (Job Description)፣ ውጤቶችና ተግባራት፣ የሥራ ባህርይ መገለጫዎች፣ የሥራ ግንኙነት እና ፈጠራዎች፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነት፣ የአእምሮ፣ ሥነ ልቦና፣ እይታ፣ አካል ጥረቶች፣ የሥራ አከባቢ ሁኔታ፣ ሥጋትና አደጋዎች እንዲሁም በመኝታ አገልግሎት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ዙርያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
መምህር ረዳኢ አክለውም፤ ሠራተኞቹ ዩኒቨርሲቲው የሠጣቸውን የሥራ ኃላፊነት በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ መብታቸውና ግዴታቸው እንዲወጡና የተቋሙን የመማር ማስተማር ሂደት የተሳካ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና ማበርከት አለባችሁ ብለዋል።
በግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናው ከተሳታፊዎች ጋር በተደረገ ውይይት የአስተዳደር መሥሪያ ቤት አገልጋይ እና ተገልጋይ ሕጋዊ አንድምታ፣ የህይወት ክህሎት እና የሥራ መደብ ዝርዝር መግለጫ በሚመለከታቸው አካላት ማብራሪያ እና ምላሽ ተሰጥቷል።
በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር እና ልማት ምክትል ፕረዚደንት ልዩ ረዳት አቶ ትኩየ ደርቤ በመዝጊያ ንግግራቸው እንደዚህ ዓይነት ሥልጠናዎች አሰራራችን በማዘመን ውጤታማ አገልግሎት ለመሥጠት ትልቅ ጠቀሜታ ስላላቸው አጠናክረን እንቀጥልበታለን ብለዋል፡፡
እንዲህ ዓይነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሥራችንን በታማኝነት፣ ቅንነት፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነት ለማገልገል ትልቅ አስተዋፅኦ አለው በማለት ተሳታፊዎች ከሥልጠናው በኃላ አስተያየታቸውን ገልጸዋል።
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ታህሳስ 13/ 2017 ዓ.ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አሥፈጻሚ
*********//*****************************