በራያ ዩኒቨርሲቲ ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሥርዓት ለማረጋገጥና ለማስቀጠል እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው በ2017 ዓ.ም በትምህርት ሚኒስቴር የተመደቡለትን የዓቅም ማሻሻያ የትምህርት መርኃ ግብር (Remedial Program) ተማሪዎች ከጥር 15-16 /2017 ዓ.ም በደማቅ ሥነ ስርዓት ለመቀበል የዞኑ አመራሮች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የማኅበረሠብ ተወካዮች፣ የጸጥታና ደኅንነት አካላት፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና የተለያዩ ማሕበራት ካካተውው እና በ2013 ዓ.ም ከተቋቋመው የማኅበረሠብ ካውንስል አባላት ጋር ዛሬ ጥር 03/ 2017 ዓ/ም በመኾኒ ከተማ ውጤታማ ውይይት ተደርጓል፡፡
የራያ ዩኒቨርሲቲ ፕረዚደንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ በንግግራቸው ዩኒቨርሲቲው የማኅበረሠቡን ችግር ለመፍታት በመማር ማስተማር፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና የማኅበረሠብ አገልግሎት እንዲሁም በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ያለው ወጤታማ ስራ በመግለጽ ይህን ለማስቀጠል የዩኒቨርሲቲው አማካሪ ምክር ቤት አባላት በተማሪዎች ቅበላ ወቅት የተለመደውን አባታዊ እና እናታዊ ምክር በመለገስ እና ክትትል በማድረግ ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የራያ ዩኒቨርሲቲ ተቋማዊ ለውጥ ሥራ አሥፈጻሚ አቶ አሸናፊ ነጋ ለአማካሪ ምክር ቤቱ አባላት ባቀረቡት ጽሑፍ ራያ ዩኒቨርሲቲ በ2016 ዓ/ም እና በ2017 ዓ/ም 6 ወር የሰራቸው አንኳር ሥራዎች፣ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎች፣ ስጋቶችና መፍትሔዎች እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው የተፈጠሩ ዓቅሞች ዝርዝር ገለጻ አድርገዋል።
ከተሳታፊ አባላት ጋር በተደረገ ውይይትየሐይማኖት መሪው ሸኽ ከድር ዓብደልቃድር በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው ከአከባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመቀናጀት ሰላማዊ መማር ማስተማር እንዲኖር እየሰራ ያለው ስራ የሚደነቅ በመሆኑ እኛም ተማሪዎቻችን በደማቅ ሁኔታ እንቀበላለን ብለዋል።
የአከባቢው ማኅበረሠብ ተወካዩ መምህር ገብረሥላሴ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር፣ የተለያየ ባህልና ቋንቋ የሚያንጸባርቁ እና ከተለያየ ቦታ የሚመጡ ተማሪዎቻችን በአግባቡ ለመቀበል እና ሠላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ለዩኒቨርሲቲው እናግዛለን በማለት ሐሳባቸውን ገልጸዋል።
ከዞኑ ፍትሕ ቢሮ የመጡት አቶ ፀሃየ አለማየሁ ደግሞ በዩኒቨርሲቲው እየተሰሩ ያሉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተጠናክረው ለማስቀጠል የልህቀት ማእከል ለማድረግ የዩኒቨርሲቲው አማካሪ ምክር ቤት አባላት ድጋፋችን አጠናክረን እንቀጥልበታለን ብለዋል።
መጋቤ ሓዲስ መምህር ዕንቁ ባህሪይ ታመነ በውይይቱ ባስተላለፉት መልእክት ተማሪዎች በየሃይማኖት ተቋማታቸው በግብረ ገብነት፣ ሥነ ባህርይ፣ ሥነ ልቦና እና ሥነ ምግባር እንዲታነጹ የሃይማኖት መሪዎች ሚና ትልቅ ነው ብለዋል።
ራያ ዩኒቨርሲቲ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በአስቸጋሪ ሁኔታ ሆኖ ተማሪዎቹን በማስተማር እና በማስመረቅ የተለየ ዩኒቨርሲቲ ያደርገዋል በማለት ለቀጣይም በምርምር እና ማኅበረሠብ አገልግሎት ስራውን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ደግሞ ከዞኑ አመራር አቶ ረዳኢ ልበሎ ናቸው።
በመጨረሻም የደቡባዊ ትግራይ ዋና አሥተዳዳሪ እና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ሃፍቱ ኪሮስ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ውስጣዊ ዓቅማችን በማጠናከር እና ለሚያጋጥሙንን ተግዳሮቶች ተገቢውን ምላሽ በመስጠት በዩኒቨርሲቲው የሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማረጋገጥ እና ለማስቀጠል እንዲሁም የተመደቡልንን የዓቅም ማሻሻያ የትምህርት መርኃ ግብር (Remedial Program) ተማሪዎች በደማቅ ሥነ ስርዓት ለመቀበል ከዩኒቨርሲቲው አማካሪ ምክር ቤት አባላት ጋር ተቀናጅተን እንሰራለን ብለዋል፡፡
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ጥር 03/ 2017 ዓ.ም
ዕውቀት ለማኅበረሠባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አሥፈጻሚ
******************************************