ራያ ዩኒቨርሲቲ እና ትግራይ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ማእከል በትብብር መስራት የሚያስችላቸው የጋራ መግባቢያ ሰነድ (MoU) ተፈራረሙ

የጋራ መግባቢያ ሰነዱ (MoU) የተፈረመው ራያ ዩኒቨርሲቲ እና ትግራይ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ማእከል በብዝኃ ሕይወት ጥበቃ እና የማህበረሰብ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ዙርያ በትብብር መስራት የሚያስችላቸው ዛሬ ጥር 08/ 2017 ዓ.ም በራያ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ነው።
በፊርማ ስነ ስርዓቱ የተገኙት የራያ ዩኒቨርሲቲ ፕረዚደንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ የዓለምን የብዝኃ ሕይወት ሥርዓት መዛባት ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰና እየከፋ መምጣቱን ገልጸው የተፈጥሮ ሃብት ሚዛን ተጠብቆ እንዲቀጥልና ውስብስብ ችግሮቹን ለመቅረፍ መንግሥት፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ተመራማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው የችግሮቹን መፍትሔ ሊዘይዱ ይገባል ብለዋል።
የጋራ መግባቢያ ሰነዱን (MoU) የፈረሙት ራያ ዩኒቨርሲቲን በመወከል የአካ/ምር/ቴክ/ሽግ/ማህ/አገ/ ምክትል ፕረዚደንት ልዩ ረዳት መሐመድአወል የሱፍ (ዶ/ር) እና የማእከሉን ተወካይ አቶ ሙላታ ሐየሎም (የትግራይ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ማእከል ዳይሬክተር) ናቸው።
በፊርማ ስነ ስርዓቱ የራያ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች እና ተመራማሪዎች፣ የትግራይ ኢንስቲትዩት ማእከል ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን የትግራይ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ማእከል ዳይሬክተር አቶ ሙላታ ሐየሎም በብዝኃ ሕይወት ጥበቃ እና ስነ ቱሪዝም ዕድገት ዙርያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በስምምነቱ መሠረት ክልሉ የበርካታ ብዝኃ ሕይወት መገኛ ቢሆንም ጠብቆ ከማቆየትና ወደ ጥቅም ከመቀየር አንጻር ክፍተቶች መኖሩን እና ሁለቱም ተቋማት በብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ሥርዓት የዕቅዳቸው አካል በማድረግና ተቀናጅተው በመስራት የብዝኃ ሕይወትን ጥበቃ ዘላቂነት እንዲሁም ከብዝኃ ሕይወት የሚገኘውን ጥቅም ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ለማሕበረሰብ ማጋራት “ማን ምን ይስራ!” የሚል ውጤታማ የሥራ ክፍፍል ተደርጓል።
በመርኃ ግብሩ ከተሳታፊዎች ጋር በተደረገ ውይይት ለብዝኃ ሕይወት መጥፋትና መመናመን መንስዔ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታትና ዘላቂ የሆነ ለውጥ ለማምጣት የአመለካከት፣ የፖሊሲ፣ የአሠራሮችና መሠረታዊ የሆኑ የአስተዳደራዊ መዋቅሮች ለውጥ፣ ባህላዊ ዕውቀቶችን ከቴክኖሎጂው ጋር ማጣመር እንዲሁም የአካባቢ ማኅበረሰብን ተሳታፊ ማድረግ ለብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ወሳኝ መሆኑን ተገልጿል።

ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ጥር 08/ 2017 ዓ.ም
ዕውቀት ለማኅበረሠባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አሥፈጻሚ
******************************************