ራያ ዩኒቨርሲቲ በትምኅርት ሚኒስቴር የተመደቡለትን የ2017 ዓ.ም የዓቅም ማሻሻያ የትምኅርት መርኃ ግብር (Remedial Program) ተማሪዎች ጥር 15 እና 16 /2017 ዓ.ም በተሳካ መንገድ ተቀብሎ ጥር 20 /2017 ዓ.ም ደግሞ መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደቱን (DOCO) በድምቀት ካስጀመረ በኃላ ዛሬ ጥር 24/ 2017 ዓ/ም ይፋዊ የ “እንኳን ደኅና መጣችሁ!” መርኃ ግብር አዘጋጅቷል።
በመርኃ ግብሩ የራያ ዩኒቨርሲቲ ፕረዚደንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ ለተማሪዎቹ “እንኳን ደኅና መጣችሁ!” በማለት ራያ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ጥራት የማይደራደር ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ገልጸው እንደ ማሳያ ያነሱት ባለፈው ዓመት በጥር እና ሰኔ / 2016 ዓ.ም ተምረው ከተፈተኑ የዓቅም ማሻሻያ የትምኅርት መርኃ ግብር (Remedial Program) ተማሪዎች 96% እና 97.55% በማሳለፍ ከሃገራችን ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበናል።
ፕሮፌሰር ታደሰ አያይዘው እንደገጹት የ2017 ዓ.ም የዓቅም ማሻሻያ የትምህርት መርኃ ግብር (Remedial Program) ተማሪዎቻችን ለማብቃት እና 100 % ለማሳለፍ ተቀናጅተን እንሠራለን በማለት ተማሪዎች ትምህርታችሁ ላይ ብቻ ትኩረት አድርጋችሁ በትምህርታችሁ ስኬታማ በመሆን እንደ የባለፈው ዓመት የመርኃ ግብሩ (Remedial Program) ተፈታኞች 100% ለማለፍ የላቀ ትጋት እንደሚጠበቅባቸው እና ውጤቱ የተሳካ እንዲሆን ዩኒቨርሲቲው በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።
የደቡባዊ ትግራይ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እና የራያ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ሃፍቱ ኪሮስ ለተማሪዎቹ ባስተላለፉት መልእክት በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ውጤታማ ሥራዎች በመስራት በፍጥነት እያደገ ወደ እሚገኝ ራያ ዩኒቨርሲቲ “ተማሪዎቻችን እንኳን ደህና መጣችሁ!” በማለት ዩኒቨርሲቲው እናንተን ለማብቃት ዝግጁ በመሆኑ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ቆይታችሁ ውጤታማ ለመሆን የዩኒቨርሲቲው ህግ ማክበር፣ የመምህራኖቻችሁ ምክር መተግበር፣ ሰላማችሁን መጠበቅ፣ ለመተጋገዝ ጥረት ማድረግ፣ የሳይንስ ቴክኖሎጂ ተማሪዎች በመሆን ህዝባችሁ እና ሀገራችሁ ለመጥቀም ከወዲሁ ዓላማ ሊኖራችሁ ይገባል ብለዋል።
“ተማሪዎች የአገር ተረካቢዎች በመሆናችሁ ራሳችሁ ውጤታማ ለማድረግ በአዲስ መንፈስ፣ በመነቃቃትና ሥነ ምግባርን በመላበስ በመማር በትምህርት እና በሥነ ምግባር ማነጽ ይጠበቅባችኋል።” ያሉት ደግሞ የደቡባዊ ትግራይ ማይጨው ሃገረ ስብከት ዋና ጸሃፊ መጋቤ ኃዲስ መምህር ዕንቁ ባኅርይ ታመነ ናቸው፡፡
የደቡባዊ ትግራይ እስልምና ጉዳዮች ፕረዚደንት ሸኽ ከድር ሸኽ ዓብዱ በበኩላቸው “ተማሪዎች በሚኖራችሁ የዩኒቨርሲቲ ቆይታ ብዝኃ ማንነት ማክበር እና ተባብሮና ተቻችሎ የመኖር ባህልን ማዳበር ቤተሰባዊ ግንኙነትን ማጠናከር እና የማንንም ዓላማ ማሳኪያ ልትሆኑ አይገባም።” በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የራያ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕረዚደንት ነጋ ዓፈራ (ዶ/ር) ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ተማሪዎች በቅድመ ዩኒቨርሲቲ ቆይታችሁ በዕውቀት፣ ክህሎት፣ ችሎታ እና ስነ ምግባር እናንተን ብቁ ለማድረግ በመማር ማስተማር፣ መሰረተ ልማት ግንባታ፣ የካፌ፣ መኝታና ህክምና እንዲሁም የተማሪዎች ኅብረት አገልግሎቶች በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ነጋ ዓፈራ አክለው ተማሪዎች ትምህርታችሁን እንከን የለሽ በሆነ መልኩ በመከታተል፣ ውጤታማ የጊዜ አጠቃቀም በመተግበር፣ ፍጹም ጨዋነት የተላበሰ ስነ ምግባር በማንጸባረቅ፣ መምህራኖቻችሁ እና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በማክበር፣ የዩኒቨርሲቲው ህግ እና ስርዓት በማክበር እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ሙሉ ጥረት በናንተ ተማሪዎች ሙሉ ትጋትና ጥረት በመጪው ዓመት የዩኒቨርሲቲ መደበኛ የቅድመ ምረቃ ትምህርታችሁ እንድትከታተሉ እንሰራለን ብለዋል፡፡
ተማሪዎች በበኩላቸው ራያ ዩኒቨርሲቲ መመደባቸውን ደስተኞች መሆናቸውን እና ትምህርታችንን ጠንክረን ለመማር እና ውጤታማ ለመሆን ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡