ይህ የተገለጸው የራያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት እና የምርምር፣ ሕትመት፣ ሥነ ምግባር እና ሥርፀት ዳይሬክቶሬት በጋራ ባዘጋጁት እና የሚደረጉ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር ሥራዎች ውጤታማ ለማድረግ፣ የምርምር ፈንድ ለማጠናከር እና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ ትኩረቱን ያደረገ የምክክር መድረክ ከዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች፣ አመራሮች እና የሚመለከታቸው አካላት ጋር ጥር 25/ 2017 ዓ.ም በመኾኒ ከተማ በተካሄደበት ወቅት ነው።
የራያ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማኅበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕረዚደንት ዶ/ር ነጋ ዓፈራ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ የምርምር ሥራዎቻችን ውጤታማ ለማድረግ እና የተመራማሪዎቻችን ዓቅም ለማሳደግ እንዲሁም ውጤታማ አሥተዋጽኦ ለማበርከት ጭብጥ የምርምር አጀንዳዎች (Thematic Research) ላይ ትኩረት አድርገን እና የምርምር ሥነ ምግባር ተከትለን የማህበረሰባችን ዕምቅ ሃብት በማጥናት ትልቅ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በጭብጥ የምርምር አጀንዳዎች እና አቅጣጫዎች (Thematic Research Areas and Principles) መሰረት በማድረግ የጭብጥ የምርምር አጀንዳዎች (Thematic Research) ምንነት፣ ዓላማ፣ ባህሪያት፣ አስፈላጊነት፣ አተገባበር፣ መርኅ፣ የበጀት አጠቃቀም፣ የግብአትና መሰረተ ልማት አጠቃቀም፣ ይዘት፣ ሂደት፣ የምርምር ንድፈ ሃሳብ አጻጻፍ እንዲሁም የራያ ዩኒቨርሲቲ ጭብጥ የምርምር አጀንዳዎች እና ሃገራዊ የምርምር ስትራቴጂ ማዕቀፍ በተመለከተ በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማኅበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕረዚደንት ልዩ ረዳት መሐመድአወል የሱፍ (ዶ/ር) በዝርዝር ቀርቧል።
የራያ ዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትሥሥር ዳይሬክተር መምህር አስመረት ኪዳነ በበኩላቸው የራያ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር አማካሪ መዋቅር፣ ዓላማ፣ ጠቀሜታ እና የሚሰራቸው ዝርዝር ተግባራት እና ኃላፊነቶች ገለጻ ያደረጉ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው የምርምር ሥነ ምግባር እና ግምገማ ኮሚቴ ተጠሪ የሆኑት መምህር ግርማይ አብርሃ (ረዳት ፕሮፌሰር) የኮሚቴው ጠቀሜታ፣ ሥራና ኃላፊነት፣ የምርምር ሥነ ምግባር መርኆችና ውሳኔዎች ትግበራ፣ የግምገማ ሂደትና ውሳኔዎች አቅርበዋል።
የራያ ባህል እና ምርምር ማዕከል ዓላማ፣ ሥራና ኃላፊነት፣ አመክንዮ፣ አሥተዋጽኦ፣ የባለድርሻ አካላት አጋርነት እና ትሥሥር፣ በማዕከሉ የተሠሩ እና በቀጣይ የሚሠሩ ሥራዎች ደግሞ በማዕከሉ አሥተባባሪ መምህር ካሕሳይ ቸኮለ (ረዳት ፕሮፌሰር) ዝርዝር ገለጻ በማድረግ የዩኒቨርሲቲው ሃገር በቀል ዕውቀቶች ምርምር አስተባባሪ መምህር ኪሮስ ጸጋይ (ረዳት ፕሮፌሰር) ደግሞ በሃገር በቀል ዕውቀቶች፣ ሥርዓት፣ ምርምር፣ ፈጠራ እና ልኅቀት ግንባታ ዙርያ ያሉ መሠረተ ሐሳቦች፣ ሥራና ኃላፊነት፣ አሥተዋጽኦ፣ ተግዳሮቶች፣ መልካም ተሞክሮዎች፣ ዲጂታላይዜሽን፣ ጥበቃ፣ ቀጣይ አጀንዳዎች እና እርምጃዎች ዝርዝር ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የምርምር አለምአቀፋዊ ግንኙነትና አጋርነት ዳይሬክተር ዶ/ር አስመላሽ ጣሰው (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ጠንካራ ዓለም አቀፋዊ አጋርነት እና ትሥሥር መፍጠር ለምርምር ፕሮጀክት ያለውን አሥተዋጽኦ ያቀረቡ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው የምርምር፣ ሕትመት፣ ሥነ ምግባር እና ሥርፀት ዳይሬክተር መምህር ተመስገን ተስፋይ (ረዳት ፕሮፌሰር) በምርምር ኅትመቶች እና ማበረታቻዎች መመሪያ፣ ዓላማ፣ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች እና መፍትሔዎቻቸው ዙርያ ገለጻ አድርገዋል።
ከምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች ጋር በተደረገ ውይይት የተለያዩ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ተነስተው በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እና ማብራሪያ ተሠጥቷል።
በመጨረሻም የራያ ዩኒቨርሲቲ ፕረዚደንት የተከበሩ ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ በመዝጊያ ንግግራቸው የምርምር ሥራዎቻችን በታማኝነት እና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመስራት ራሳችን፣ ማህበረሰባችን እና ሃገራችን በመጥቀም ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነታችን ማረጋገጥ ይጠበቅባቹኃል በማለት በምርምር፣ ኅትመት፣ የምርምር ሥነ ምግባር፣ ፈንድ በማፈላለግ ረገድ ራሳችሁን ለማብቃት ብርቱ ጥረት እንደሚያስፈልግ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ጥር 25/ 2017 ዓ.ም
ዕውቀት ለማኅበረሠባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አሥፈጻሚ
*****************************************