በዞኑ ሕገ ወጥ የወጣቶች ዝውውር የሚያስከትለውን ዘርፈ-ብዙ ችግሮች ለመፍታት የተቀናጀ እና ተግባር ተኮር የባለ ድርሻ አካላት ሚና እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

ራያ ዩኒቨርሲቲ ከትግራይ ወጣቶች ቢሮ ጋር በመተባበር በደቡባዊ ትግራይ ዞን ሕገ ወጥ የወጣቶች ዝውውርን ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ማህበራዊ፣ ስነ ልቦናዊ፣ ፖለቲካዊ፣ አካላዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ቀውሶች ለመፍታት ተቀናጅቶ መስራት በሚቻልበት መንገድ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ዛሬ መጋቢት 25/ 2017 ዓ.ም በመኾኒ ከተማ የምክክር መድረክ አካሄደ።
በዞኑ ሕገ ወጥ የወጣቶች ዝውውር የተማረ፣ አምራች እና ሀገር ተረካቢ የሆነውን የሰው ኃይል እያሳጣ መሆኑን የገለጹት የደቡባዊ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የራያ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ሃፍቱ ኪሮስ በዞኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ሕገ ወጥ የወጣቶች ዝውውር እና የሚያስከትለውን ቀውስ ለመከላከል ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተን እንሰራለን ብለዋል።
የራያ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክተር መምህር ደባሲ ግደይ በበኩላቸው፤ ራያ ዩኒቨርሲቲ የአከባቢውን ማህበረሰብ ችግሮ ለመፍታት የተለያዩ ስራዎች እየሰራ መሆኑን በመግለፅ ወጣቶች በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ስደት እንዲሄዱ የሚያደርጋቸው ምክንያት በመለየት ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በቅንጅት ይሰራል በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዩኒቨርሲቲው የስነ ማህበረሰብ (Sociology) ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ቸኮለ ሓድስ ደግሞ፤ ሕገ ወጥ የወጣቶች ዝውውር ምንነት፣ መንስኤዎች፣ እና የሚያስከትለውን ቀውስ በማቅረብ በተለይ የሚታየውን የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ስራ አጥነት፣ የአቻ ግፊት፣ ድህነት፣ ጦርነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በዞኑ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር አድርጎታል ብለዋል።
በምክክር መድረኩ ሕገ ወጥ የወጣቶች ዝውውርን ለመከላከል ሊደረጉ የሚገባቸው ቁልፍ ተግባራት እና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ዝርዝር ሙያዊ ማብራሪያ ያቀረቡት በዩኒቨርሲቲው የስነ ዜጋ እና ሰነ ምግባር ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር ግርማይ ሃይለኪሮስ፤ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በዞኑ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማህበራዊ ጫና ከማሳደሩም ባሻገር ወጣቶች ለአካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት እየዳረገ እንደሚገኝ አውስተዋል።
ሕገ ወጥ የወጣቶች ዝውውርን በማህበረሰቡ ዘንድ እያስከተለ ያለውን ጉዳት በመገንዘብ እና ችግሩን ለመግታት ወጣቶች ራሳቸው እንዲችሉ ሰፊ እና የተቀናጀ ስራ ይሰራል ያሉት የደቡባዊ ትግራይ ዞን ማሕበራዊ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ረዳኢ ልበሎ ናቸው።
የትግራይ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ሀላፊ ዶ/ር ገብሩ ካሕሳይ በመድረኩ፤ ሕገ ወጥ የወጣቶች ዝውውርን ለመከላከል የመንግስት፣ ህዝብ፣ የሚድያ ባለሙያዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው እና እንደ ሀገር ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ለውጥ ማምጣት ፥ ምቹ ሁኔታን በሀገር ውስጥ መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል። የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ራያ ዩኒቨርሲቲ በሕገ ወጥ የወጣቶች ዝውውር አጀንዳ ሁሉን የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የሚያነቃቃ የምክክር መድረክ ማዘጋጀቱን ያመሰገኑት በትግራይ ክልል ሕገ ወጥ የወጣቶች ዝውውር አሰተባባሪ አቶ ግርማይ ገብረሥላሴ፤ በክልሉ ሕገ ወጥ የወጣቶች ዝውውርን ለማስወገድ ወጣቶች ስለ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አስከፊነት ተገንዝበው የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ እና የወጣቶች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት በመስራት እንዲፈቱ እንደሚሰራ ሀሳባቸውን አቅርበዋል።
ከተሳታፊዎች ጋር በተደረገ ውይይት መድረኩ ወቅታዊ እና አስፈላጊ መሆኑን እና በዞኑ ሕገ ወጥ የወጣቶች ዝውውርን በዘላቂነት ለመፍታት የስራ እድል በማስፋት ወጣቶች በአገራቸው ሰርተው እንዲለወጡ አመለካከታቸውን ለመቀየር የተቀናጀ እና ተግባር ተኮር ስራ መሰራት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
በመድረኩ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የትግራይ ክልል ኮሙኒኬሽን እና ወጣቶች ግብርና አመራሮች እና ባለሙያዎች፣ የዞኑ እና ወረዳ አመራሮች እና ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ሀገር በቀል ግጭት ፈቺ አካላት፣ የማህበረሰብ ተወካዮች፣ ወጣቶች፣ የችግሩ ሰለባ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ የፍትሕ አካላት፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
********************
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ መጋቢት 25/ 2017 ዓ.ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
********************